ዳኞች በማያቋርጥ ሒደት ብቃታቸውን ሊያሳድጉና በሥልጠና ሊያልፉ እንደሚገባ ተጠቆመ
/ Categories: News

ዳኞች በማያቋርጥ ሒደት ብቃታቸውን ሊያሳድጉና በሥልጠና ሊያልፉ እንደሚገባ ተጠቆመ

ዳኞች በማያቋርጥ ሒደት ብቃታቸውን ሊያሳድጉና በሥልጠና ሊያልፉ እንደሚገባ ይህም የዳኝነት ነጻነትን ለማስጠበቅና ክህሎታቸውን ለማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ም/ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ተþሊት ይመስል ገለጹ፡፡

ከፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት፣ ከፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት እና ከፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የተውጣጡ 350 ያህል የፌደራል ፍ/ቤቶች ዳኞች የተሳተፉበት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ከነሐሴ 21-22 ቀን 2014 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ተካሒዷል፡፡

ክቡር ም/ፕሬዚደንቱ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የአገራችን መገኛኛ ብዙኃን በፍ/ቤት የሚታዩ ክፍተቶችን ከመጠቆም ባሻገር የዳኞችን ድካምና ልፋት በትክክል ሊያሳዩ ወይም ሊዘግቡ ይገባል፣ መገናኛ ብዙኃኑ በማስረጃ ያልተደገፈና ሙያዊ ኃላፊነት የጎደለው ዘገባ ከማሰራጨትም ሊታቀቡ ይገባል ብለዋል፡፡

ፍርድ ቤትና ዳኞች ስለሰጡት ውሳኔ ትክክለኛነት የማስረዳት ግዴታ የለባቸውም ያሉት ም/ፕሬዚደንቱ፣ ስህተት ካለ በይግባኝ፣ የዳኛ ተጠያቂነት ካለ ደግሞ በዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የሚታይ መሆኑን አስምረውበታል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚደንት ክብርት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ በሥልጠናው ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር በ2014 በጀት ዓመት በፌደራል ፍ/ቤቶች ጥሩ አፈጻጸም የተመዘገበ መሆኑን አንስተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፍርድ ቤቱን አፈጻጸም አስመልክቶ በራሱ ያስጠናው ጥናት ፍርድ ቤቱ በገለልተኛ አካል ካስጠናው የጥናት ውጤት ጋር ተቀራራቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዳኝነት ጥራትን ማረጋገጥ ፍርድ ቤቶች ያልተሻገሩት ተግዳሮት መሆኑን ጠቁመው በዚህ ዙሪያ በሶስቱ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የአቻ ግምገማ (Peer Review) በማድረግ ችግሮች ካሉ ግብረ-መልስ እንዲሰጥባቸው ማስቻል በዘርፉ ያለውን ችግር ለማስተካከል አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በተዘዋዋሪ ችሎት አማካኝነት ጥሩ ሥራ የተከናወነ መሆኑንና ነገር ግን ችግሩ በጣም ሰፊ ከመሆኑ አንጻር የፌደራል ፍርድ ቤቶችን በየአካባቢው ማቋቋም አስፈላጊ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

ለፌደራል ፍርድ ቤት ዳኞች በተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ላይ ከተዳሰሱ ርዕሠ-ጉዳዮች መካከል "በሰብዓዊነት ላይ ስለሚፈጸሙ ወንጀሎች ክስ በኢትዮጵያ ያለው አተገባበር እና ተግዳሮቶች" በሚል ርዕስ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምሕር በሆኑት ዶ/ር ማርሸት ታደሰ ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን "በዳኝነት ሙያ ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው የተግባቦት ክህሎት እና የተግባቦት ሥነምግባር መርሆዎች" በሚል ርዕስ ደግሞ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ም/ፕሬዚደንት እና የፌደራል ፍ/ቤቶች ቃል አቀባይ በሆኑት በክቡር አቶ ተስፋዬ ንዋይ ቀርቦ በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በሌላ በኩል በኢሞሽናል ኢንተለጀንስ ላይ ያተኮረና ሳይንሳዊ ይዘት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ማብራሪያ ደግሞ በዶ/ር ምህረት ደበበ ቀርቦ በፍ/ቤቱ ዳኞች የሀሳብ ልውውጥ ተደርጎበታል፡፡ በሥልጠናው ላይ የችሎት አዳራሾች ከዳኞችም ሆነ ከባለጉዳዮች የሚመነጩ የተለያዩ ስሜቶች (emotions) የሚስተናገዱባቸው መድረኮች በመሆናቸው እነዚህን የስሜት አይነቶች ተቆጣጥሮ ሥራን በአግባቡ ማከናወን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ግንዛቤ ያስጨበጠ ማብራሪያ ቀርቧል፡፡ 

"በዳኝነት ሙያ ውስጥ የቡድናዊ ሥራ ውጤታማነትን ለማጎልበት የሚረዱ መርሆዎችና ተሞክሮዎች"  በሚል ርዕሰ-ጉዳይ ላይ ደግሞ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ዳኛ በሆኑት በክቡር ብርሀኑ አመነው ማብራሪያ ቀርቧል፡፡ ማብራሪያው የቡድናዊ ሥራን ከፍርድ ቤት ችሎቶች አወቃቀርና አሠራር ጋር በማስተሳሰር የቀረበ ሲሆን በማብራሪያው ላይ የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ከተሳታፊ ዳኞች ቀርበው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

  የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

 

Previous Article የፍርድ ቤቱ ዳኞች እና የአስተዳደር ዘርፍ የሥራ ክፍሎች በ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና በ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ግምገማ አካሔዱ
Next Article የፍርድ ቤቱ ሠራተኞች ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀንን አከበሩ
Print
63