ዳኞች የዕግድ አሰጣጥና አፈጻጸምን በሚመለከቱ ሕጎች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ በየጊዜው ሊያዳብሩ እንደሚገባ ተጠቆመ
/ Categories: News

ዳኞች የዕግድ አሰጣጥና አፈጻጸምን በሚመለከቱ ሕጎች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ በየጊዜው ሊያዳብሩ እንደሚገባ ተጠቆመ

ዳኞች ከአገር ኢንቨስትመንት፣ ከሕዝብ ጥቅም እንዲሁም ከግለሰብ ክርክሮች ጋር በተያያዘ   በዕግድ አሰጣጥና አፈጻጸም ዙሪያ የሚወስኑትን ጉዳይ ማየትና መፈተሽ እንዲሁም በሕጎች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ በየጊዜው ሊያዳብሩ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

ይህ የተገለጸው ከሶስቱ ፌደራል ፍርድ ቤቶች ለተውጣጡ ዳኞች ከዕግድ አሰጣጥና አፈጻጸም ጋር በተያያዘ በፌደራል ፍርድ ቤቶች የተዘጋጀውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡

ክቡር ም/ፕሬዚደንቱ ተከራካሪ ወገኖች ከገንዘብ፣ ከንብረት እንዲሁም ከሌሎች የፍትሐብሔር ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ወደፍርድ ቤት ሲያቀርቡ ክርክሮች ረጅም ጊዜ የሚወስዱ ከመሆናቸው አንጻር በክርክሩ ሒደት ሊወሰንበት የሚችል የተከራካሪ ወገን ንብረቱን እንዳያሸሽና ለሌላ ሶስተኛ ወገንም እንዳያስተላልፍ ንብረቶቹ ተከብረው የሚቆዩበት ሁኔታ በእኛ ሀገርም ሆነ በሌሎች ሀገራት ሕግ ላይ ተደንግጎ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

ዕገዳን በተመለከተ የተደነገጉ ሕጎች በሚተረጎሙበትና ተግባራዊ በሚደረጉበት ወቅት በተለያዩ ዳኞች የተለያየ አተረጓጎም ተግባራዊ እንዳይሆን ውይይት ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ በፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ላይ ዕግድን በተመለከተ በተቀመጡ ድንጋጌዎች አፈጻጸም ላይ የተወሰኑ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ጠቁመዋል፡፡

ተከራካሪ ወገኖች ሙግትን ወደፍርድ ቤት ሲያመጡ በግለሰቦች፣ በመንግስት ተቋማት እና በመንግስት የልማት ድርጅቶች ላይ ክስ ሊመሰርቱ እንደሚችሉ የገለጹት ክቡር ም/ፕሬዚደንቱ፣ በዚህ ሒደት ውስጥ ለተወሰነ የገንዘብ ጥቅም ሲባል የሌላውን ተከራካሪ ወገን አጠቃላይ የንግድ ጥቅምና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚገድብ ዕግድ የሚሰጥበት ሁኔታ የሚታይ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በተለይም ከግንባታ እና ከመንገድ ሥራ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ አገራዊ ፋይዳ ባላቸው ፕሮጀክቶች ጋር በተገናኘ ለተወሰኑ የገንዘብ ጥቅሞች በሚሰጥ ዕግድ በቢሊዮኖች በሚቆጠር የገንዘብ መጠን እንቅስቃሴ የሚያደርጉ የመንገድ ፕሮጀክቶች ታግደው የሚቆዩበት አሠራር በመኖሩ ምክንያት የፕሮጀክቶቹ ወጪ እስከሶስት እና አራት እጥፍ ድረስ ሊጨምር እንደሚችል መረጃ ያላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይህ የተጋነነ ወጪ በግብር ከፋዩ እና በሀገሪቱ ላይ ጫና እንደሚያሳድር ገልጸው በግለሰቦች መካከልም በሚደረግ የሕግ ክርክር በንብረትና በገንዘብ ላይ የሚሰጡ እግዶች በኢኮኖሚው ውስጥ ሊያመነጩ በሚችሉት ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

በዚህ መሠረት እግድ የሚሰጡ ዳኞች ሕግን እና ሕግን መሠረት አድርገው ውሳኔ ሲሰጡ በዕግድ አሰጣጥ ሒደት እነዚህ ችግሮች እንዳይከሰቱ በሕጎቹ ላይ የሚኖርን ግንዛቤ ማየትና መፈተሸ በየጊዜውም ማዳበር እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

በዕግድ አሰጣጥና አፈጻጸም ላይ የተዘጋጀውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና የሰጡት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት ዳኛ ተሾመ ሽፈራው ናቸው፡፡

የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናው በቡድን ውይይት የታገዘ ሲሆን ከተሳታፊ ዳኞች ለቀረቡ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶችም ከመድረክ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ነጻና ገለልጸኛ ፍርድ ቤት ለህግ የበላይነት!

የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የፌዴራል ፍርድ ቤት መር አስማሚነት መመሪያ አወጣ
Next Article ክስ የተቋረጠባቸው ሶስት የክስ መዝገቦች የስነ-ስርዓት ሂደቶች ላይ የተሰጠ የፕሬስ መግለጫ
Print
117