ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሙስና ተግባራት መከላከያና መቆጣጠሪያ ስትራቴጂ ይፋ አደረገ
/ Categories: News

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሙስና ተግባራት መከላከያና መቆጣጠሪያ ስትራቴጂ ይፋ አደረገ

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያዘጋጀውን እና በፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ውይይት ተደርጎበትና ቅቡልነት አግኝቶ ለትግበራ ዝግጁ የሆነውን “በዳኝነት አካል ውስጥ የሚታዩ የሙስና ተግባራት መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ስትራቴጂ” የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አመራሮች፣ የምድብ ችሎት ተጠሪ ዳኞች፣ ሰብሳቢ ዳኞች፣ የዳኞች ተወካዮች እና የአስተዳደር ዘርፍ ልዩ ልዩ የስራ ክፍል ሃላፊዎች በተሳተፉበት የውይይት መድረክ ይፋ አድርጓል፡፡

ስትራቴጂው ይፋ የተደረገበት የውይይት መድረክ ለስትራቴጂው አተገባበር የሚገጁ ሃሳቦችን በማንሸራሸር ይሁንታ ለመስጠት የተዘጋጀ ነው፡፡

ስትቴጂውን ለመተግበርና የሚጠበቀውን ከሙስና የጸዳ የዳኝነት አገልግሎት የመስጠት ውጤት ለማግኘት አጠቃላይ የፍርድ ቤቱ ማህበረሰብና የባለድርሻ አካላት እንዲወያዩበትና የጋራ መረዳት እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚያስችል መርሃ ግብር መዘጋጀቱም ተጠቁሟል፡፡

ላለፉት ሶስት ዓመታት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ነጻነታቸውን ለማስጠበቅ እና ለማረጋገጥ የተሰራ መሆኑን እና ውጤት የተገኘበት እንደሆነ የገለጹት የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በዘንድሮው እና ወደፊት በሚመጣው ጊዜ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ሰርዓት መዘርጋትና መተግበር ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ምክትል ፕሬዝደንት በበኩላቸው የሙስና ተግባራት መከላከያና መቆጣጠሪያ ስትራቴጂው የዳኞችን ነጻነት የሚጋፋ ሳይሆን ይበልጥ የሚያጠናክረው ነው ካሉ በኋላ ስትራቴጂውን በመተግበር ፍርድ ቤቶቻችንን ከሙስና ተጋላጭነት ልንታደጋቸውና የህዝብ አመኔታ የሚጊለብትባቸው እንዲሆኑ የፍርድ ቤቱ ማህበረሰብ በሙሉ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የስትራቴጂ ሰነዱ ይዘትን አስመልክቶ የፌ/መጀ/ደ/ፍ/ቤት ም/ፕሬደንትና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ቃል አቀባይ ክቡር አቶ ተስፋዬ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በተሳታፊዎችም ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

የውይይት መድረኩን የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጽ/ቤት ከጠቅላይ ፍ/ቤት ጋር በመተባበር አዘጋጅተውታል፡፡

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article በፌደራል ፍርድ ቤቶች የተገልጋዮች የእርካታ ደረጃ በአማካይ 78 በመቶ መሆኑን ጥናት አመለከተ
Next Article በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የተቀናጀ የጉዳዮች አስተዳደር መረጃ ስርዓት (ICMIS) እና ኤሌክትሮኒክ-ሰነድ አስተዳደር ስርዓት (e-RMS) ልማትና ትግበራ ጽንሰ-ተልዕኮ (Inception Mission) መርሃ ግብር ተካሄደ
Print
33