ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የፌዴራል ፍርድ ቤት መር አስማሚነት መመሪያ አወጣ
/ Categories: News

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የፌዴራል ፍርድ ቤት መር አስማሚነት መመሪያ አወጣ

በፍትሃብሔር ጉዳዮ በተከታካሪ ወገኖች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን በስምምነት መፍታት የሚሰጠው ጥቅምና ለፍትሕ ሥርዓቱ መጎልበት ያለውን አስተዋጽኦ በተለይም በተከራካሪዎ መካከል ቀጣይነት ያለው መልካም ግንኙነት እንዲኖር ለማስቻል ተከራካሪዎቹ ራሳቸው አለመግባባቶቻቸውን ለመፍታት በስምምነት መጨረስ ያለውን አስተዋጽኦ  ከግምት በማስገባት፤

በፍርድ ቤቶች ላይ የሚኖር የመዝገብ መደራረብ ምክንያት ጉዳዮች እልባት ሳያገኙ የሚዘገዩበትን ሁኔታ ለመቀነስ አንዳንድ የፍትሐብሔር ጉዳዮችን በስምምነት መፍታት ለባለጉዳዮች አማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓትን የበለጠ ተደራሽ በማድረግ፣ ፈጣን የሆነ የፍትሕ ስርዓትን ለማስፈን ስለሚያስችል፤

አስማሚዎች መብቶቻቸውን እና ሃላፊነታቸውን ተረድተው የማስማማት ተግባራቸውን በጥራት፣ በብቃት እና ምክንያታዊ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያከናውኑ የስነ-ምግባር መርሆች እና ዲስፕሊን ስነ-ስርዓቶችን መደንገግ አስፈላጊ በመሆኑ፤

የፍርድ ቤት መር አስማሚነትን የሚያግዝ የአስማሚዎችን የዲሲፕሊን ጉዳዮች የሚመረምር ኮሚቴ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 45(7) መሰረት መቋቋም ስለሚያስፈልገው እና የኮሚቴውንም ዝርዝር ሃላፊነት፤ አወቃቀር እና የተጠያቂነት ወሰን መደንገግ ስለሚያስፈልግ፤

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 45(8) እና 48(4) በተሰጠው ስልጣን መሰረት የፍርድ ቤት መር የአስማሚነት መመሪያ ወጥቷል፡፡

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያወጣው መመሪያ የፌዴራል ፍርድ ቤት መር አስማሚነት መመሪያ ቁጥር 12/2014 በሚል ስያሜ ይጠራል፡፡ 

የመመሪያውን ዲጂታል (ፒዲኤፍ) ቅጂ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረ-ገጽ እና ቴሌግራም ቻናል ወይም ከታች በተቀመጠው ማስፈንጠሪያ ያገኙታል፡፡

https://t.me/fscethiopiaPR/74

ነጻና ገለልተኛ ፍ/ቤት ለህግ የበላይነት!

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article ባለፉት ሶስት ዓመታት በተከናወኑ የማሻሻያ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤት መገኘቱ ተገለጸ
Next Article ዳኞች የዕግድ አሰጣጥና አፈጻጸምን በሚመለከቱ ሕጎች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ በየጊዜው ሊያዳብሩ እንደሚገባ ተጠቆመ
Print
1232