ፍርድ ቤቱ ለአራት ክልሎች ጠቅላይ ፍ/ቤቶች የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
/ Categories: News

ፍርድ ቤቱ ለአራት ክልሎች ጠቅላይ ፍ/ቤቶች የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አራት የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶችን ለማጠናከር ዛሬ የካቲት 9 ቀን 2014 ዓ.ም የሰባት ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡

የቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገላቸው በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው ለአማራ እና ለአፋር ክልሎች ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች እንዲሁም በቅርቡ በአዲስ መልክ በክልልነት የተቋቋሙትን የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶችን ለማጠናከር ነው፡፡

በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት በክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ጽ/ቤት በተካሔደው የዕርዳታ ርክክብ ሥነሥርዓት ላይ የአማራ፣ የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ፕሬዚደንቶች ተገኝተው እርዳታውን ተረክበዋል፡፡

በርክክብ ሥነሥርዓቱ ላይ ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ባደረጉት ንግግር በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን እና በአዲስ መልክ የተቋቋሙ ክልሎችን ፍርድ ቤቶች ወደፊትም ለመደገፍ ፍርድ ቤቱ ጥረት እንደሚያደርግ ገልጸው ተቋማቸው ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ ዩ.ኤን.ዲ.ፒ እና ለሌሎችም ዓለም አቀፍ ተቋማት ጠቅላይ ፍ/ቤቶችን እንዲደግፉ ጥያቄ መቅረቡን ጠቁመዋል፡፡

ዕርዳታው የተሰባሰበው የፌደራል ፍርድ ቤቶች ካላቸው ሀብት ላይ ተቀንሶ ሲሆን በአብዛኛው የኮምፒዩተር፣ ፕሪንተር፣ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን እና ቀለሞችን ያካተተ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡

ድጋፉ የተበረከተላቸው የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች በስራቸው ለሚገኙ ፍርድ ቤቶች በጦርነቱ የደረሰባቸውን የጉዳት መጠን እና ሰፋት ከግንዛቤ በማስገባት እንዲሁም አዲስ በመደራጀት ላይ የሚገኙት የሁለቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤቶችም በስራቸው የሚገኙ የዞንና የወረዳ ፍ/ቤቶች ያለባቸውን የቁሳቁስ እጥረት ታሳቢ በማድረግ የሚከፋፈል እንደሚሆን በርክክብ ሥነሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡

ድጋፉ የተበረከተላቸው የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንቶች በሰጡት አስተያየት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ያለባቸውን ችግር አሳሳቢነት በመገንዘብ ለሰጠው ምላሽ በክልሎች ስም ምስጋናቸውን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት የደረሰ ጉደትን በተመለከተ ሁኔታዎች ሲፈቅዱ የደረሰው የጉዳት መጠን ታይቶ አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግ እንደሚችል በመድረኩ ላይ ክብርት ፕሬዚደንትዋ ገልጸዋል፡፡

========= /// ==========”

Previous Article የፌደራል ፍርድ ቤቶችን የዳኝነት ነጻነት፣ ገለልተኝነት እና ተጠያቂነትን ለማጠናከር የተወሰዱ እርምጃዎች
Next Article የፍርድ ቤቱ አስተዳደር ዘርፍ አፈጻጸም ከፍተኛ መሻሻል ያሳየ መሆኑ ተገለጸ
Print
1958