ፍርድ ቤቱ በስትራቴጂያዊ እና ዓመታዊ ዕቅዱ ላይ ለምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ማብራሪያ ሰጠ
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፍትህና የዲሞክራሲ ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ፍርድ ቤቱ ባዘጋጀው ሶስተኛው ስትራቴጂያዊ ዕቅድ እና ዓመታዊ ዕቅድ ላይ ማብራሪያ ሰጠ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በፍርድ ቤቱ በኩል ዕቅዶቹን አስመልክቶ ሰፊ ማብራሪያ ከመቅረቡ በፊት በሰጡት አጭር ገለጻ የዳኝነት ዘርፉ በአማካሪ ድርጅት በመታገዝ ስትራቴጂያዊ ዕቅዱን ማዘጋጀቱን፤ የዕቅዱን ይዘትና አዘገጃጀት ሂደት የሚከታተል በየደረጃ ያሉ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አመራሮች፣ የስራ ክፍል ኃላፊዎችና ባለሙያዎች አባል የሆኑባቸው ዓቢይና ቴክኒክ ኮሚቴ መቋቋማቸውን፤ በረቂቅ ዕቅዱ ላይ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማህበረሰብ እና ባለድርሻ አካላት መወያየታቸውን እና የተገኙ ተጨማሪ ግብዓቶችን በማካተት ተዘጋጅቶ የጸደቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ክብርት መዓዛ የፍርድ ቤቱ ዕቅድ አንድ ወጥ የስራ አመራር መሳሪያ እና ሞዴል አለመጠቀሙን እና ከተቋማዊ ባህሪው ጋር የሚጣጣም ውህድ የስራ አመራርና የዕቅድ ሞዴል መከቱሉንም አመልክተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ተጠሪነቱ ለተከበረው ምክር ቤት ቢሆንም ዓመታዊ ዕቅዱን እና አፈጻጸሙን ለህዝብ ይፋ የሚያደርግበት ዓመታዊ “የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አሁናዊ ሁኔታ” ሃገራዊ መድረክ እንደሚያዘጋጅም አክለው ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት እና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ቃል አቀባይ ክቡር አቶ ተስፋዬ ነዋይ የስትራቴጂያዊ ዕቅዱን አስመልክቶ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ አቶ ተስፋዬ በሰጡት ማብራሪያ ስትራቴጂያዊ ዕቅዱ 6 ቁልፍ የውጤት መስኮች፤ 13 ግቦች እና 33 ማስፈጸሚያ ስትራቴጂዎች ያሉት መሆኑን ገልጸው፤ የትግበራ ክትትልና ግምገማ ስርዓቱን አስረድተዋል፡፡
የህግ፣ ፍትህና የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በበኩሉ ዕቅዱን ሲገመግም የታዘባቸውን ጠንካራ ጎኖችና ቢካተቱ ያላቸውን ውስን ነጥቦች ገልጿል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው በህገ መንግስቱ እና በምክር ቤቱ የአሰራርና የአባላት ስነምግባር ደንብ በተሰጠው ስልጣንና ሃላፊነት መሰረት የሚያካሂደውን የክትትል፣ የቁጥጥርና የድጋፍ ተልዕኮውን የሚወጣበት መርሆች እና ስልቶች በመርሃ ግብሩ ላይ ለተገኙ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አመራሮች አስተዋውቋል፡፡
በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ ባቀረበው የዕቅድ ማብራሪያ ላይ እና ትኩረት አድርጎ ሊሰራባቸው ይገባሉ ያሏቸውን አቅጣጫዎች የቋሚ ኮሚቴው አባላት የተጠቆሙ ሲሆን ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ቋሚ ኮሚቴው ክትትልና ቁጥጥር ሲያደርግ የዳኝነት ነጻነትና ገለልተኝነት ላይ ተጽዕኖ በማያሳድር መልኩ መሆን እንዳለበት አሳስቧል፡፡
ተቋማዊ ነጻነቱ የተረጋገጠ ፍርድ ቤት መኖር ለዜጎች ዋስትና ነው ያሉት የፍርድ ቤቱ አመራሮች፤ ምክር ቤቱ የዳኝነት ዘርፉ የተሰጠውን ህገመንግስታዊ ተልዕኮ መወጣት የሚያስችለው አቅም እንዲኖረው ከበጀት ጀምሮ የራሱ የሆነ አገልግሎት መስጫ ህንጻዎች እና መሰረተልማት እንዲሟሉለት በማድረግ ድጋፉን እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
ክብርት ወ/ሮ መዓዛ በማጠቃለያቸው ፍርድ ቤቱ ምክር ቤቱ በሚያስቀምጣቸው አቅጣጫዎች መሰረት የጋራ ራዕያቸውን ለማሳካት አብረው የሚሰሩ መሆኑን እና የምክር ቤቱ አባላት እና የህግ ስፈጻሚው ከፍተኛ ባለስልጣናት ፍርድ ቤቶች የሚሰሩባቸው መርሆች እና በፌዴራል መንግስት መዋቅር ውስጥ ያላቸው ቦታ እና የተሰጣቸው ተልዕኮን የሚያስተዋውቁ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች የሚዘጋጁ መሆን ጠቁመዋል፡፡
ነጻና ገለልተኛ ፍርድ ቤት ለህግ የበላይነት!
የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት
ታህሳስ 8 ቀን 2014 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤
130