ፍርድ ቤቱ በአገልግሎት አሰጣጥ መልካም ተሞክሮ ለመቅሰም የመስክ ጉብኝት አደረገ
/ Categories: News

ፍርድ ቤቱ በአገልግሎት አሰጣጥ መልካም ተሞክሮ ለመቅሰም የመስክ ጉብኝት አደረገ

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሬጂስትራር አገልግሎትን ለማሻሻል የሚያስችለውን መልካም ተሞክሮ ለመቅሰም በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉብኝት አደረገ፡፡

የመልካም ተሞክሮው ጉብኝት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ሃላፊ በክቡር አቶ ቦጃ ታደሰ አስተባባሪነት የተዘጋጀ ሲሆን ይህም በፍርድ ቤቱ የሚሰጠውን የዳኝነት አገልግሎት ቅልጥፍና ለማሻሻል ትኩረት የሚሻውን የሬጂስትራር አገልግሎት የተገልጋይ ጊዜን፣ ገንዘብንና እንግልትን በመቀነስ የመረጃ እና ተግባቦት ቴክኖሎጂ (Information Communication Technology) በመጠቀም መስጠት የሚያስችውን የአሰራር ስርዓትና አደረጃጀት ተሞክሮ መቅሰም አስችሎታል፡፡

በመልካም ተሞክሮው ጉብኝት የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ጋዛሊ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሚመሩት የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአሰራር እና የአደረጃጀት መልካም ልምድ ለመቅሰም ስለመረጣቸው ያላቸውን አክብሮትና ምስጋና አቅርበው በፍርድ ቤቱ እየተካሄደ ያለው የለውጥና የማሻሻያ ስራ አንድ ጊዜ ተሰርቶ የሚጠናቀቅ ሳይሆን በየጊዜው እና በየዘርፉ የሚከናወን አዳጊና ቀጣይናት ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ፍርድ ቤቶቹ የክልል እና የፌዴራል ተብለው በሃገራችን የመንግስት መዋቅር ከመከፋፈላቸው በስተቀር የሚያገለግሉት ህዝብን ነው ያሉት ክቡር አቶ ጋዛሊ አንዳችን ከሌላችን በመማር በመርህና በውጤቱ አንድ አይነት የሆነውን የዳኝነት አግልግሎት ዘርፍ ጊዜው የሚጠይቀውን የህዝቡን ፍትህ የማግኘት መብት የማረጋገጥና የህግ የበላይነትን የማስጠበቅ ተልዕኳችንን ማሳደግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

በመልካም ተሞክሮው ጉብኝት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የማሻሻያ ስራዎች ቅኝነት ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ እና ማሻሻያው ትኩረት ያደረገባቸው ዘርፎችን የሚጠቁም ገለጻ ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የችሎት አገልግሎት ማለትም ፋይል ከመክፈት ጀምሮ ውሳኔ ግልባጭ እስከመስጠት ድረስ ያለውን አሰራር፤ የመዝገብ አያያዝ እና በክልሉ በዞን ወረዳ፣ ከፍተኛና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች መካከል ስለሚደረግ የመዝገብ ቅብብሎሽ የተመለከቱ ተግባራትን ቀልጣፋና በእንድ ማዕከል አገልግሎት ለማከናወን ያስቻላቸው አደረጃጀትና አሰራር ላይ መረጃ የሚሰጥ ገለጻም ቀርቧል፡፡ በጉብኝቱ ከተሳተፉ የሬጂስትራር እና የዳታቤዝ ባለሙያዎች እንዲሁም አመራሮች ገለጸውን መሰረት በማድረግ ለአነሷቸው ተጨማሪ ማብራሪያ ለሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች መልስ ተሰጥቷል፡፡

ይንንም ተከትሎ አንድ ባለጉዳይ የዳኝነት አገልግሎቱን ለማግኘት መጀመሪያ ጥያቄ ማቅረብ ከሚጀምርበት የመረጃ ክፍል ጀምሮ ፋይል መክፈት፤ ትዕዛዝ፣ እግድ፤ ውሳኔ ግልባጭና የመዝገብ ግልባጭ በአጭር ሰአት ማግኘት የሚችልበት የአሰራር ሂደትን በአስረጂ እንዲጎበኙ ተደርጓል፡፡ እንደየአገልግሎት ዓይነቱ የተደራጁ ቡድኖች እና የህግ ባለሙያዎች (Legal Officers) ስለሚያከናውኗቸው ተግባራት ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

በጉብኝቱ የተሳተፉ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የሬጂስትራር ባለሙያዎች በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤትባካሄዱት የመልካም ተሞክሮ ጉብኝት የሚሰጡትን አገልግሎት ለማሻሻል የሚረዳቸው አሰራር የቀሰሙ መሆኑን ገልጸው አሁን በስራ ላይ ያለው አሰራር በአግባቡ በተዘጋጀ ደንብና ማኑዋል መሻሻል እንዳለበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ተመሳሳይ መልካም ተሞክሮ መቅሰሚያ ጉብኝት ለቀሪ ሬጅስትራር ባለሙያዎች የሚካሄድ መሆኑንም ከፕሬዝደንት ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የጀመራቸውን የአገልግሎት አሰጣጥ የማሻሻያ ስራዎች እውን ለማድረግ የውጭ ሃገራትንና የክልል ፍርድ ቤቶችን መልካም ተሞክሮ እየቀሰመ ከፍርድ ቤተ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሀዋሳ ማዕከል በይፋ አገልግሎት መስጠት ጀመረ
Next Article ፍርድ ቤቶች በዘጠኝ ወሩ ከአንድ መቶ 19 ሺህ በላይ ለሆኑ መዛግብት እልባት ሰጡ
Print
420