ፍርድ ቤቱ ባቀረበው የበጀት ጥያቄ ላይ በምክር ቤቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጠ
/ Categories: News

ፍርድ ቤቱ ባቀረበው የበጀት ጥያቄ ላይ በምክር ቤቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጠ

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን የ2014 በጀት ዓመት የበጀት ፍላጎት ለኢፌዲሪ ሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ማቅረቡን ተከትሎ በበጀት ፍላጎት ላይ ለተነሱ ማብራሪያ ለሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች መግለጫ ሰጠ፡፡

በኢፌዲሪ የህዝብ ጉዳዮች ምክር ቤት የገቢ፤ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በቀረበ የበጀት ፍላጎት ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ እንዲረዳው ከፍርድ ቤቱ አመራሮች ተጨማሪ ማብራሪያ ለመሰብሰብ ግንቦት 12 ቀን 2013 ዓ.ም በምክር ቤቱ አዳራሽ ውይይት አካሂዷል፡፡

በጠቅላይ ፍርድ ቤት በአምስት ፕሮግራሞች የተዘጋጀው የበጀት ፍላጎት መግለጫ በገንዘብ ሚኒስቴር የበጀት እቅድ አዘገጃጀት ስርዓት ከተቀመጠው ጣራ በላይ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ይህ የሆነበትን ዋና ምክንያት በአመራሮቹ አማካኝነት ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በ2013 ዓመት የነበራቸውን ጠንካራ አፈጻጸም ጠብቀው እና አጎልብተው ለማቆየት እንዲሁም ያሉትን ክፍተቶች አስተካክለው በ2014 ዓ.ም ውጤታማ፤ ቀልጣፋ እና ተዓማኒነት ያለው የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት እና በተሸሻለው አዋጅና እና በተጀመሩ የለውጥ ስራዎች በቀጣይ ዓመት ለመተግበር የታሰቡ ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ የተዘጋጀ ዕቅድ መሆኑን ገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ ቋሚ ኮሚቴው በገንዘብ ሚኒስቴር ከተቀመጠቅ የበጀት ጣራ አንጻር ከፍተኛ የልዩነት የታየባቸው የካፒታል በጀት ፍላጎቶች ምክንያታዊነት፤ ከግማሽ  በጀት ዓመት የካፒታል በጀት አፈጻጸም አንጻር የተጠየቀውን በጀት ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም ያለ አቅም እና ዝግጁነት፤ ከህንጻ ግንባታ ጋር ተያይዞ የቀረበ የበጀት ፍላጎት፤ የዋና ኦዲተር የኦዲት ግኝቶች ላይ የማስተካከያ እርምጃ ስለመወሰዱ እና የንብረት አያያዝና አወጋገድ ጋር ተያይዞ ያሉ አፈጻጸሞችን የተመለከተ ዝርዝር መረጃ እንዲሰጠው በሶስቱም ፌዴራል ፍርድ ቤቶች ላይ ማብራሪያ ጠይቋል፡፡

የፍርድ ቤቱ አመራሮች በገንዘብ ሚኒስቴር ከተቀመጠው ጣሪያ በላይ የበጀት ፍላጎት የቀረበበትን ምክንያት ሲያስረዱ በቅርቡ ምክር ቤቱ ያጸደቃቸው የዳኝነት አስተዳደር እና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጆች አተገባበር አዳዲስ አገልግሎቶችን፤ አደረጃጀቶችን እና ግብአቶችን የሚጠይቁ ናቸው፡፡  በዳኝነት ዘርፉ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ቅልጥፍና፤ ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ፤ በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ለማስደገፍ እና የህዝብ አመኔታን ለማጎልበት የሚረዱ የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ስራዎችን ለመስራት እንዲሁም ፍርድ ቤቶች የራሳቸው መገለጫና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት መስጫ ህንጻዎችን ለመገንባት የተቀረጹ ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠልና ለማስጀመር ነው ሲሉ ጥልቅ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በተጨማሪም ፍርድ ቤቶች ለዘመናት የተከማቸ የመሰረተ ልማት ችግር ያለባቸው መሆኑን በመግለጽና እነዚህን ችግሮች ከአሁን ጀምሮ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ካልተጀመረ ፍርድ ቤቶች በህገመንግስቱ የተሰጣቸውን ዳኝነት የመስጠት ተልኳቸውን እንዳይወጡ ያደርጋቸዋል፡፡  ፍርድ ቤቶች በሃገራችን የህግ በላይነትን የማረጋገጥ፤ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ እና ለዘላቂ ልማት ዋስትና የሚጠበቅባቸውን ሚና በተገቢው ሁኔታ እንዳይጫወቱ ያደርጋቸዋል፡፡  ስለሆነም ምክር ቤቱ ይህንን ተረድቶ ፍርድ ቤቶችን በልዩ ሁኔታ በበጀት የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡

ከገንዘብ ሚኒስቴር የባለሙያ ምክር ለመስጠት የተገኙት ባለሙያዎች ፍርድ ቤቶች በበጀት ምደባና አስተደደር ድጋፍ ልዩ ድጋፍ ከሚደረግላቸው ዘርፎች መካከል መሆኑን ገልጸው መንግስት ከተለያዩ ምንጮች የሚያገኘውን ካፒታል ቅድሚያ ለሚያስፈልጓቸው ጉዳዮችን በመለየት በቁጠባና በውጤታማነት  መጠቀም የሚያስፈልግ መሆኑን ጠቁመው  ፍርድ ቤቶች መንግስት ቀዳሚ ትኩረት ቢሰጣቸውም ፍርድ ቤቶች በጀት የሚጠይቁባቸው ፕሮጀክቶችና ፕግራሞች መካከል ቅድሚያ ትኩረት ማግኘት ያለባቸውን በበጀት መደገፍ ይገባል ብለዋል፡፡  ሃገሪቱ ያላትን ሀብት የምታስተዳድበትን ህግ ደንብና መመሪያን በጥብቅ በመከተል የበጀት ድልድሉ ይሰራልም ሲሉ ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ 

በውይይቱ ማጠናቀቂያ የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፍርድ ቤቶችን የመንግስት አቅም በፈቀደ መጠን በበጀት ለመደገፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት በመግለጽ በበጀት ጥያቄው መስተካከል አለባቸው ተብለው የተለዩ ጉዳዮች ላይ ማስተካከያ ተደርጎ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለምክር ቤቱ እንዲቀርብ የጋራ ስምምነት ላይ ተደርጓል፡፡

በውይይት መድረኩ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዝደንቶችና ም/ፕሬዝደንቶች እንዲሁም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ልዩ ልዩ ክፍል ኃላፊዎች በፍርድ ቤት በኩል የተሳተፉ ሲሆን በምከር ቤቱ በኩል ደግሞ የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል፡፡

የፌዴራል መንግስት ከፍተኛው የዳኝነት አካል የሆነው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን ዓመታዊ በጀት እያዘጋጀ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚያቀርብ፤ ሲጸድቅም በተግባር ላይ እንደሚያውል በኢፌዲሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 79 ቁጥር 6 ላይ በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

Previous Article የተማሪዎችን የሕግ ግንዛቤ ለማሳደግ የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ
Next Article የተሻሻሉት የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እና የዳኝነት አስተዳደር አዋጆች መጽደቃቸው ለፍርድ ቤቱ የሪፎርም ሥራ መሠረት መሆናቸው ተገለጸ
Print
1863