Friday, March 22, 2024 / Categories: News ፍርድ ቤቱ አዲስ ከተሾሙ ዳኞች ጋር የስራ ማስጀመሪያ እና የትዉዉቅ ፕሮግራም አደረገ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አዲስ ከተሾሙ የፍርድ ቤቱ ዳኞች ጋር መጋቢት 12 ቀን 2016 ዓ.ም የስራ ማስጀመሪያ እና የትዉዉቅ ፕሮግራም አድርጓል፡፡ በፕሮግራሙ ተገኝተዉ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ፍርድ ቤቱ በያዘዉ የ5 ዓመት የስትራቴጅክ እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ እየተገበራቸዉ ያሉ ዋና ዋና ስራዎችን ለማስተዋወቅ ታስቦ የተዛጋጀ መድረክ መሆኑን ገልፀዉ ተሿሚ ዳኞች ከዉስጥና ከዉጭ ተጽዕኖዎች በፀዳ መንገድ በግልፅ ችሎት በማስቻል ምክንያታዊ ፣ጥራት ያለዉ እና ተገማች ዉሳኔ በመወሰን እንዲሁም ለሌሎች ዳኞች ተጨማሪ ጉልበት በመሆን ቦታዉ የሚፈልገዉን ትዕግስትና ስነ ምግባር ተላብሰዉ በህግና ህሊና ሚዛን በመጠቀም የህዝብ አመኔታ ያተረፈ ፍርድ ቤት ለማድረግ እንዲሰሩ ክቡር ፕሬዝደንቱ አደራ ብለዋል፡፡ በፍርድ ቤቱ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን እየተሰሩ ያሉ ሰፊ የቴክኖሎጂ ስራዎችን ፣ከኢንስፔክሽን ስራ ክፍል ጋር በተገናኘ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎችና ግኝቶች፣የጉዳዮች ፍሰት ምንነትና አተገባበር፣ የሬጅስትራር አገልግሎት አሰጣጥ እና የችሎት አደረጃጀት እንዲሁም የስትራቴጅክ አመራር የስራ ክፍል የ2016 በጀት ዓመት እቅድ፣የክትትልና የግምገማ ስርዓት በየስራ ክፍሎቹ ኃላፊዎች የቀረበ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በቀድሞዉ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ፅ/ቤት ኃላፊ እና በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶ/ር ጌታሁን አለማየሁ የሰበር ስነ-ስርዓት መመሪያ ላይ አጠር ያለ ገለፃ ቀርቧል፡፡ በመድረኩ በቀረቡ ገለፃዎች ላይ ሰፊ ዉይይት የተደረገ ሲሆን ከዳኞች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበዉ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በመጨረሻም ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነባር ዳኞች እና የስራ ኃላፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ እና የእርስ በእርስ ትዉዉቅ ተደርጓል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ለአዲስ ተሿሚ ዳኞች መልካም የስራ ዘመን ይመኛል፡፡ Previous Article የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስራ ሃላፊዎች የፕሮጀክት አስተዳደር ስልጠና Next Article በረቂቅ የህፃናት ፍትህ የስልጠና ሞጁል ላይ የግብአት ማሰባሰቢያ ዉይይት ተደረገ Print 4910