"ፍርድ ቤቱ አገልግሎት ፈላጊዎችን በተሻለ ለማስተናገድ የሚረዱ ስራዎች ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል"-የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
/ Categories: News

"ፍርድ ቤቱ አገልግሎት ፈላጊዎችን በተሻለ ለማስተናገድ የሚረዱ ስራዎች ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል"-የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አገልግሎት ፈላጊዎችን በተሻለ መልኩ ለማስተናገድ የሚረዱ የለውጥ ስራዎች ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የምክር ቤቱ የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት በመገኘት የመስክ ምልከታ አካሂዷል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በፍርድ ቤቱ ውስጥ የፍርድ አሰጣጥ ሂደት፣ ወረፋ መጠበቂያ ስርዓት፣ ችሎት ማስቻያ ቦታዎችን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን ጎብኝተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት ከሰራተኞች፣ ዳኞችና የፍርድ ቤቱ የበላይ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን በድክመትና በጥንካሬ የተለዩ ጉዳዮች ላይም ተወያይተዋል።

በፍርድ ቤቱ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የዳኞች ቁጥርና መዝገብ አለመመጣጠን፣ የሰራተኞች ፍልሰትና የተቀላጠፈ አገልግሎት በሚፈለገው መልኩ አለመስጠት ከተነሱት ችግሮች መካከል ናቸው።

የህግና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እጸገነት መንግስቱ እንደተናገሩት፤ ፍርድ ቤቱ ግልጽ ችሎት ማስቻል ላይ የበለጠ መስራት ይገባዋል።

“በተለይም ዜጎች በፍጥነት ፍትህ እንዲያገኙ ከማድረግ አኳያ ብዙ ስራ ይጠበቃል” ያሉት ሰብሳቢዋ ይህን ለማድረግ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ፍርድ ቤቱ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት በሚያደርገው ጥረት ፖሊስንና ፍትህ ሚኒስቴርን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር አለበት ሲሉም አክለዋል።

ፍርድ ቤቱ ለሙስና በር ሊከፍቱ የሚችሉ አሰራሮችን ከማጥራትና የመፍትሄ እርምጃዎችን ከመውሰድ አኳያም የበለጠ መስራት እንደሚጠበቅበት ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ቋሚ ኮሚቴው ፍርድ ቤቱ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች የተሻሉ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ሲሉም አረጋግጠዋል።

EBC

Previous Article በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሕጎችና አዋጆች ሲወጡ ልዩ ትኩረት የሚፈልጉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ
Next Article በፍርድ ቤቱ አዲስ ተሿሚ ፕሬዚደንቶች እና በቀድሞ ፕሬዚደንቶች መካከል የሥራ ርክክብ ሥነሥርዓት ተፈጸመ
Print
428