ፍርድ ቤቱ እና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የመግባቢያ ስምምነት  ተፈራረሙ
/ Categories: News

ፍርድ ቤቱ እና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

የፈደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንሰቲትዩት በቴክኖሎጂ ዘርፍ አብሮ ለመስራት የሚያስችልላቸውን የመግባቢያ ስምምነት በፍርድ ቤቱ የስብሰባ አዳራሽ መጋቢት 14 ቀን 2015 ዓ.ም ተፈራረሙ።
የመግባቢያ ስምምነቱን በፈደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኩል የፈረሙት የፍ/ቤቱ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ሲሆኑ በኢንስቲትዩቱ በኩል ደግሞ የኢንሰቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ወርቁ ጋቸና ናቸው።
በመግባቢያ ስምምነቱ መሠረት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንሰቲትዩት የፌደራል ፍርድ ቤት ተገልጋዮች ባሉበት ሆነው ስለጉዳያቸው በቂ መረጃ እንዲያገኙ የሚያስችል እና የባለጉዳዮችን መዛግብት በዲጂታል ዘዴ በቀላሉ ለማግኘት የሚረዳ መተግበሪያ (Chat box and File tracing application) የሚያበለጽግ ይሆናል ።
ስምምነቱ ከዚህ በተጨማሪ ኢንስቲትዩቱ ለፍርድ ቤቱ የሪፖርት ማቅረቢያ እና የተገልጋዮችን ቅሬታ ለመቀበል የሚረዳ ዲጂታል ቴምፕሌት (Report maker application and Complaint handling application) ለማበልጸግ የሚያስችለዉ ይሆናል።
በመግባቢያ ስምምነቱ የፊርማ ሥነሥርዓት ላይ የፍ/ቤቱ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ባደረጉት ንግግር ፍርድ ቤቱ አሁን ካሉበት ችግሮች በተጨማሪ በቀጣይም ያሉበትን ችግሮች ለይቶ የቴክኖሎጂ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸዉ መሆኑን ሲያረጋግጥ በሁለቱ ተቋማት የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ፍ/ቤቱን የቴክኖሎጂ መፍትሔ እንዲያገኝ የሚያስችለው መሆኑን ገልፀው፣ የተደረሰውን ስምምነት እንደ አንድ የችግር መፍቻ ቁልፍ አድርገው እንደሚወስዱት አስገንዝበዋል።
Previous Article በፌደራል ፍርድ ቤቶች የአስተዳደር ሠራተኞች ረቂቅ ደንብ ይዘት ላይ ለቋሚ ኮሚቴ አባላት ማብራሪያ ተሰጠ
Next Article የፍርድ ቤት ተገልጋዮችን እንግልት የሚቀንሱ እና የፍትሕ እርካታ የሚጨምሩ የማሻሻያ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ተገለጸ
Print
1776