ፍርድ ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሴቶችና ሕጻናት ሥርዓተ-ችሎት እንዲዘጋጅ እየሰራ እንደሚገኝ ተጠቆመ
/ Categories: News

ፍርድ ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሴቶችና ሕጻናት ሥርዓተ-ችሎት እንዲዘጋጅ እየሰራ እንደሚገኝ ተጠቆመ

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሴቶችና ሕጻናት ዙሪያ የሚኖርን የፍትሕ ተገማችነትን ለማስፋት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ሥርዓተ-ችሎት እንዲዘጋጅ እያደረገ እንደሚገኝ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ አስታወቁ፡፡

ም/ፕሬዚደንቱ ይህን ያስታወቁት የፌደራል ፍ/ቤቶች ዓለም ዓቀፍ ፀረ-ጾታዊ ጥቃት ቀንን ሕዳር 30 ቀን 2014 ዓ.ም በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት አዳራሽ በፓናል ውይይት ሲከበር ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ነው፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የፀረ-ማግለልና ወሲባዊ ትንኮሳን የተመለከተ የፖሊሲ ሰነድ አዘጋጅቶ በቅርቡ ሥራ ላይ የሚያውል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የፍ/ቤቱ ሥራ የዳኝነት ሥራ እንደመሆኑ መጠን የሴቶችንና ሕጻናትን ጥቃት በተመለከተ ከወንጀል ምርመራ እና ክስ አመሠራረት ጋር በተያያዘ በሕክምና ማስረጃ ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮች ውጤታማ ዳኝነት ለመስጠት አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳላቸው በመግለጽም ፍ/ቤቱ ይህን ለመቅረፍ ከወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ዋነኛ አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሠራር ለመፍጠር ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ም/ፕሬዚደንቱ አክለውም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ቅድመ-ዝግጅታቸው እየተጠናቀቀ ከሚገኙና በፍ/ቤቱ እንዲተገበሩ ከታቀዱ ተግባራት መካከል ከአቅም ውሱንነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች፣ የወንጀል ምርመራና የማስረጃ ሥነሥርዓት፣ ለጾታዊ ጥቃት ሰለባዎች ሊሰጥ ስለሚገባው የሥነልቦና ድጋፍ እና ሥልጠናዎች በከፍተኛ የትምሕርት ተቋማትና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች እንዲሰጡ የማድረግ ሥራ እንደሚገኝበት ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ ላይ «ጾታዊ ጥቃት በሴቶችና በሕጻናት ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖ» በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጽሑፍ በፍ/ቤቱ የሴቶችና ወጣቶች ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የወጣቶች ጉዳይ ቡድን መሪ በሆኑት በአቶ አሌክሳንደር አዳም የቀረበ ሲሆን የቤት ውስጥ ጥቃት በፌደራል ፍርድ ቤቶች የሚታይበትን ሁኔታ በተመለከተ በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የሥርዓተ-ጾታ ፕሮጀክት አስተባባሪ በሆኑት በወ/ሮ ፍሬሕይወት አራርሳ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

ይህን ተከትሎም የፓናል ውይይት ተደርጓል፡፡ በውይይቱ ዓለም አቀፍ መርሆዎችን ታሳቢ በማድረግ የቤት ውስጥ ጥቃት ወንጀልን ለመዳኘት ፍርድ ቤቶች ምን ማድረግ ይችላሉ በሚል ነጥብ ዙሪያ ማብራሪያ ቀርቧል፡፡

የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ሥልጣን ሥር የሚወደወቁትን የቤት ውስጥ ጥቃት ወንጀሎችን በሴቶችና ሕጻናት ችሎት የሚታዩበት ዕድል ስለመኖሩ፣ ለጥቃቱ ወጥ የሆነ ምላሽ ለመስጠት በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ሥልጣን ስር የሚወድቁ የቤት ውስጥ ጥቃት ወንጀሎችን ለማየትና ከስር ፍ/ቤት በይግባኝ የሚመጡትን ለማየት ልዩ ችሎት በማቋቋም አስፈላጊነት ላይ እንዲሁም ጉዳዩ በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ስለሚታይበት ሁኔታ በፓናል ውይይቱ ላይ ሽፋን ተሰጥቶታል፡፡

የፓናል ውይይቱን የመሩት የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ም/ፕሬዚደንት ወ/ሮ አሸነፈች አበበ ሲሆኑ ማብራሪያ ያቀረቡት ደግሞ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ዳኛ ወ/ሮ እትመት አሰፋ፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ዳኛ ወ/ሮ አመለወርቅ ግዘቸው፣ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ዳኛ ወ/ሮ አሳሂብ ብዙነህ እንዲሁም በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የሕጻናት ፕሮጀክት ጽ/ቤት አስተባባሪ አቶ ልዑለስላሴ ሊበን ናቸው፡፡

በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የሴቶችና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት በተዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ የፌደራል ፍ/ቤት ዳኞች፣ ሬጅስትራሮች፣ የሥራ ኃላፊዎች፣ ቡድን መሪዎች እና ከፀጥታ ተቋማት ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article የክብርት ፕሬዝደንቷ ጉብኝት በድሬደዋ ምድብ ችሎቶች
Next Article የሙስና ወንጀልን በትብብርና በአንድነት መንፈስ መከላከል እንደሚገባ ተገለጸ
Print
948