ፍርድ ቤቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ
/ Categories: News

ፍርድ ቤቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የሁለቱን ተቋማት የትብብር መስክ ያጠናክራል የተባለ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

በስምምነቱ ተቋማቱ ከዚህ ቀደም የነበራቸዉን ስምምነቶች በአዲስ መልክ ቅርፅ በማስያዝ እና አዳዲስ የትብብር መስኮችን በማካተት በየኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ቤት በኩል ችግር ፈቺ እና ዘላቂነት ያላቸው የጥናት እና ምርምር እንዲሁም የትምህርት እና ስልጠና ዘርፍ ላይ በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል፡፡

ተቋማቱ በዚሁ የመግባቢያ ስምምነት ማዕቀፍ መነሻነት ከህግ ትምህርት ዘርፍ ባሻገር በዩኒቨርሲቲው ስር ከሚገኙ የተለያዩ የትምህርት ክፍሎች ጋር በመተባበር የዳኝነት ስርዓቱን ለማዘመን እና ለማጠናከር በሚረዱ እና የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ ተግባር ተኮር እና ችግር ፈቺ ስራዎችን ለማከናወን ተስማምተዋል፡፡

በፊርማ ስነ ስርዓቱ ወቅት ንግግር ያደረጉት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ሁለቱ ተቋማት ከዚህ ቀደም በርካታ ስራዎችን በትብብር ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ገልፀው ይህ ስምምነት የነበረውን ስራ የሚያጠናክር እና የትብብር አድማሱን በማስፋት በተለያዩ መስኮች ለሁለቱም ተቋማት በተለይም ለዳኝነት ስራ መሻሻል የሚጠቅሙ የጥናት እና ምርምር ስራዎች እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው የሁለቱ ተቋማት በትብብር መስራት የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል እና ማህበረሰብ አቀፍ የሆኑ አገልግሎቶችን ለማስፋት እንደሚረዳ በመግለፅ ከህግ ትምህርት ቤት ጋር የተጀመረው ስራ ከሌሎች የትምህርት ክፍሎችም ጋር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የመግባቢያ ስምምነት ፊርማ ስነ ሰርዓቱ ላይ ከሁለቱ ተቋማት ፕሬዚዳንቶች በተጨማሪ ምክትል ፕሬዚዳንቶች እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

Previous Article የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ልዑካን በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመገኘት ጉብኝት አደረጉ
Next Article የኢ-ፋይሊንግ እና የፕላዝማ ችሎት የስራ ማስጀመሪያ መርሃግብር ተካሄደ
Print
890