Wednesday, April 5, 2023 / Categories: News ፍርድ ቤቱ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ያደረገው ስምምነት የፍርድ ቤቱን ማሕበረሰብ ጫና ለመቀነስና አገልግሎቱን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገለጸ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከኢትዮጵያ ቴሌኮም ጋር የተፈራረመው የመግባቢያ ስምምነት (Memorandum of Understanding) በዳኝነት አገልግሎት አሠጣጥ ዘርፍ የተሰማሩ የፍርድ ቤቱን ዳኞችና ሌሎች ባለሙያዎች ጫና ለመቀነስና የፍ/ቤቱን አገልግሎት ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ገለጹ፡፡ሁለቱ ተቋማት የፌደራል ፍርድ ቤቶችን አገልግሎት አሠጣጥ በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ለዜጎች ተደራሽ፣ ቀልጣፋ እና ፈጣን አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ መጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል በተካሔደ ሥነሥርዓት ከስምምነት ደርሰዋል፡፡በፍርድ ቤቱ በኩል በስምምነት ሰነዱ ላይ ፊርማቸውን ያስቀመጡት የፍ/ቤቱ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ባደረጉት ንግግር በሁለቱ ተቋማት መካከል የተደረሰው ስምምነት የፌደራል ፍርድ ቤቶች ምድብ ችሎቶችን እርስ በርስ በዲጂታል ዘዴ በማስተሳሰር በመካከላቸው የሚደረገውን የመረጃ ልውውጥ ቀላል እንደሚያደርገው አስረድተዋል፡፡በተጨማሪም ስምምነቱ ተገልጋዮች ባሉበት ቦታ ሆነው የዳኝነት አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል በመሆኑ ይህም የፍትሕ ተደራሽነቱን አንድ እርምጃ ወደፊት እንደሚወስደው ገልጸው፣ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡ በቴክኖሎጂ የታገዘ መሆኑ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ስለሚያስችል የተገልጋዮችን እርካታ የሚያሳድግ ይሆናል ብለዋል፡፡ በኢትዮ ቴሌኮም በኩል ስምምነቱን የፈረሙት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ት ፍሬሕይወት ታምሩ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር በስምምነቱ መሠረት ፍርድ ቤቱ አገልግሎት አሠጣጡን በዲጂታል ዘዴ ተደራሽ ለማድረግ መሠረተ-ልማት ከመዘርጋት ባሻገር በሚዘረጋው መሠረተ-ልማት አማካኝነት ከፍተኛ የመረጃ ልውውጥ የሚደረግ ከመሆኑ አንጻር አገልግሎት አሠጣጡ ደህንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ በስምምነቱ መሠረት ኢትዮ ቴሌኮም ለፍ/ቤቱ አስተማማኝና ደረጃዉን የጠበቀ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) መሰረተ ልማት ማለትም አስተማማኝ የሀይል አቅርቦት፤ የመጠባበቂያ ኔትዎርክና የኔትዎርክ ደህንነት ያለዉ ዘመናዊ የሞጁላር መረጃ ማእከል (Modular Data Center)፤ የኔትዎርክ ኦፕሬሽን መቆጣጠሪያ ማእከል (Network Operation Center) የዋይድ ኤሪያ እና ሎካል ኤሪያ ኔትዎርክ ግንባታ እንዲሁም የሶፍትዌር ደረጃ ዋይድ ኤሪያ ኔትዎርክ ማስተዳደሪያ (SD-WAN) ዓለም አቀፍ ደረጃዉንና ጥራቱን ጠብቆ በመገንባት ያስረክባል፡፡ ይህም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተግባራዊ በሚያደርገዉ የኢ-ኮርት ሲስተም አማካኝነት በፌደራል ፍርድ ቤቶች የሚሰጡ የዳኝነት አገልግሎቶች ለተገልጋዮች ቀልጣፋ፤ ዉጤታማ፤ ዘመናዊና ተደራሽ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው፡፡ከዚህ በተጨማሪም ስምምነቱ ከዚህ ቀደም በሁለቱ ተቋማት መካከል የነበሩትን የቴሌኮም አገልግሎቶች የትብብር ስራዎችን በተጠናከረ ሁኔታ ተፈጻሚ ለማድረግ በተለይም በሁለቱ ተቋማት መካከል የአቅም ግንባታ፤ የስልጠና፤ የእዉቀት፤ የክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሚያስችል ለመረዳት ተችሏል፡፡ፍርድ ቤቱ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡን ተደራሽ፣ ቀልጣፋና በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ ቀደም ሲል ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና ከኢትዮ ፖስታ ጋር የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረመ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ Previous Article የፍርድ ቤት ተገልጋዮችን እንግልት የሚቀንሱ እና የፍትሕ እርካታ የሚጨምሩ የማሻሻያ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ተገለጸ Next Article የፍርድ ቤቱ አዲስ ተሿሚ ፕሬዝዳንቶች እና በቀድሞ ፕሬዝዳንቶች መካከል የስራ ርክክብ ተፈጸመ Print 1505