Wednesday, January 4, 2023 / Categories: News ፍርድ ቤቱ ከጾታዊ ጥቃት ነጻ የሆነ ማህበረሰብ የመገንባት ዓላማ እንዳለዉ ተገለጸ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከጾታዊ ጥቃት ነጻ የሆነ ማህበረሰብ የመገንባት ዓላማ ያለው መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ ገለጹ፡፡ «ጾታን መሰረት አድርገዉ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ከመከላከል አንጻር የአመራሮች ሚና» በሚል ርዕስ ለፌደራል ፍርድ ቤቶች አመራሮችና ሰብሳቢ ዳኞች በቢሾፍቱ ከተማ አዱላላ ሪዞርትና ስፓ ታሕሳስ 25 ቀን 2015 ዓ.ም የተዘጋጀ የስልጠና መርሐ-ግብር ተሒዷል፡፡ ክቡር ም/ፕሬዚደንቱ በሥልጠናው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ፍርድ ቤቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ የትምህርት ክፍልና ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ጋር በመተባበር ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከል ብሎም ለመግታት የሚደረገዉ ጥረት በፌደራል ፍርድ ቤቶች ከተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች አንዱ ተግባር መሆኑን ጠቅሰዉ የስልጠና መርሐ-ግብሩ ሲጠናቀቅም ቀጣይ ምዕራፍ ወደሆነዉ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ በስልጠና መርሐ--ግብሩ ላይ በእዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነልቦና ትምሕርት ክፍል መምሕር በሆኑት በዶ/ር ማስተዋል መኮንን «የስነ-ልቦና እና ማህበራዊ ደህንነት ጽንሰ-ሐሳቦች» በሚል ርዕስ በቀረበ ማብራሪያ ላይ ሰፋ ያለ ዉይይት የተደረገ ሲሆን፤ «ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከልና የፍትህ ሂደትን ለማሳለጥ የፍትህ አመራሮች ሚና" በሚል ርዕስ ላይ በዩኒቨርሲቲው የስነልቦና ትምሕርት ክፍል መምሕር በሆኑት በዶ/ር ብርሃን ወንድሙ በቀረበ የመወያያ ሀሳብ ላይ ደግሞ ሰፊ የሐሳብ ልውውጥ ተደርጓል፡፡ በመድረኩ ላይ በተጨማሪም «የአመራር የልቦና ዉቅር» በሚል ርዕስ ለተሳታፊዎቹ ማብራሪያ ቀርቧል፡፡ በተመሳሳይም ከተለያዩ የፍትሕ ተቋማት ለተውጣጡ 70 ያህል የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች «ጾታን መሠረት ካደረገ ጉዳት ጋር በተያያዘ የሥነልቦናዊና ማሕበራዊ ድጋፎችና መርሆዎች» በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሥልጠና በሁለቱ የዩኒቨርሲቲው የስነልቦና ትምሕርት ክፍል መምሕራን በዚሁ በአዱላላ ሪዞርትና ስፓ ታሕሳስ 25 ቀን 2015 ዓ.ም ተሰጥቷል፡፡ ሥልጠናውን ያስጀመሩት የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ም/ፕሬዚደንት ክብርት ወ/ሮ አሸነፈች አበበ ሲሆኑ የሴቶች ጥቃት የግማሹ የሕብረተሰብ ክፍል ጉዳት በመሆኑ ሁሉንም ዜጋ ስለሚመለከት ተገቢውን ትኩረት ሊያገኝ ይገባዋል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ድርጊቱ እንዳይፈጸም መከላከል፣ ተፈጽሞ ከተገኘም ጉዳዩ ተገቢው የሕግ እርምጃ እንዲወሰድበት ማድረግ፣ ለተጎጅዎችም ማሕበራዊና ሥነልቦናዊ ድጋፍ እንዲያገኙ የማድረግ አስፈላጊነቱን አስምረውበታል፡፡ በሥልጠናው ላይ ከፌደራል አቃቤ-ሕግ፣ ከፌደራል፣ ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ ፖሊስ፣ ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች፣ ከሕክምና ተቋማት እንዲሁም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ከሌሎች መ/ቤቶች የተወከሉ የሥራ ኃላዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል፡፡ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት Previous Article ለፍርድ ቤቱ የአስተዳደር ሠራተኞች በንቃተ-ሕግ እንዲሁም ጾታን መሠረት ካደረገ ጉዳት ጋር በተያያዘ በሥነልቦናዊና በማሕበራዊ ድጋፎች እና መርሆዎች ላይ ሥልጠና ተሰጠ Next Article በፌደራል ፍ/ቤቶች የአምስት ዓመት ስትራትጅክ ዕቅድ ላይ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ እንደ አንድ ግብ የተቀመጠ መሆኑ ተገለጸ Print 620