ፍርድ ቤቱ የዩኒቨርሲቲ የሕግ ተማሪዎችን አቅም ለማጎልበት የሚያከናውነው ሥራ ትውልድን የማነጽ ተግባር እንደሆነ ተጠቆመ
/ Categories: News

ፍርድ ቤቱ የዩኒቨርሲቲ የሕግ ተማሪዎችን አቅም ለማጎልበት የሚያከናውነው ሥራ ትውልድን የማነጽ ተግባር እንደሆነ ተጠቆመ

የፌደራል ፍርድ ቤቶች ከሚሰጡት የዳኝነት አገልግሎት በተጨማሪ የልዩ ልዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ንቃተ-ሕግ ለማሳደግ የሚረዳ መርሐ-ግብር ቀርጸው ተግባራዊ በማድረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን የዚሁ መርሐ-ግብር አካል የሆነና «የተማሪዎች ቀን» በሚል ስያሜ የተዘጋጀ ፕሮግራም መጋቢት 10 ቀን 2014 ዓ.ም በሒልተን ሆቴል ተካሂዷል፡፡

በፕሮግራሙ ማጠናቀቂያ ላይ ክቡር ም/ፕሬዚደንቱ ባደረጉት ንግግር በቀጣይ የፌደራል ፍ/ቤት ዳኞች ሊሆኑ የሚችሉት የዛሬ የሕግ ተማሪዎች በተጨባጭ በፍርድ ቤት ውስጥ ያሉ አሠራሮችን እና ሥነሥርዓቶችን እንዲረዱ እንዲሁም ዳኞች እንዴት ጉዳዮችን እና ባለጉዳዮችን እንደሚያስተናግዱ ግንዛቤ እንዲጨብጡ የሚያስችል ፕሮግራም መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

መርሐ-ግብሩ የሕግ ተማሪዎች ትምሕርታቸውን ሲያጠናቅቁ ዳኛ ሆነው ወደፍ/ቤት ከመምጣታቸው በፊት ፍርድ ቤት ውስጥ ያለው አሠራር ምን እንደሚመስል ቀድመው ተገንዝበው ወደሙያው እንዲገቡ የሚያስችል በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በፌደራል ፍርድ ቤቶች ለሕግ ተማሪዎች የሜንተርሽፕ እና የኢንተርንሽፕ ፕሮግራም እንዲጀመር በማድረግ የነገ ዳኞችና የሕግ ባለሙያዎች የሚሆኑት የዛሬ የሕግ ተማሪዎች ከፌደራል ፍርድ ቤቶች ጋር በመቀራረብ በፍርድ ቤቶች ውስጥ የሚከናወኑ ተግባራትን እንዲያውቁ ያስቻለውን መርሐ-ግብር የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚደንት ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በማስጀመራቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የፌደራል ፍርድ ቤቶች ከፍተኛ አመራሮች፣ ዳኞች፣ ጥሪ የተደረገላቸው ግለሰቦችና የሕግ ተማሪዎች በተሳተፉበት በዚህ ዝግጅት ላይ ፍርድ ቤቱ ተግባራዊ ሲያደርግ በቆየው የሜንተርሽፕ እና የኢንተርንሽፕ ፕሮግራም ላይ የተሳተፉ ዳኞችና የሕግ ተማሪዎች ተሞክሯቸውን የሚያሳይ አጭር ፊልም ለተሳታፊዎች ቀርቧል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቴ የ5ኛ ዓመት አራት የሕግ ተማሪዎች የተሳተፉበትና «ከባድ ወንጀል ፈጻሚዎችን በዕድሜ ልክ እስራት መቅጣት ተገቢ ነው ወይስ አይደለም» በሚል ርዕስ ሙግት በምስለ ችሎት (Moot Court) የተካሔደ ሲሆን ሙግቱን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለት ዳኞችና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ት/ቤት መምሕር በመዳኘት አሸናፊዎቹ እንዲለዩ አድርገዋል፡፡ ለአሸናፊዎቹም በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡

ከመድረኩ መሪ ሐሳብ ጋር ተዛማጅነት ያላቸውና በተማሪዎች የተዘጋጁ ፎቶ ግራፎች ለዕይታ የቀረቡ ሲሆን «ፍትሕ፣ ፍርድ ቤት እና እኔ» በሚል ርዕስ በሥነጽሑፍ ውድድር አሸናፊ የሆነ ጽሑፍም ለተሳታፊዎቹ ቀርቧል፡፡

በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይ ፍርድ ቤቱ ተግባራዊ ባደረገው የሜንተርሽፕ እና የኢንተርንሽፕ ፕሮግራም ላይ ለተሳተፉ ዳኞችና የሕግ ተማሪዎች የዕውቅና መስጫ ሥነሥርዓት ተካሒዷል፡፡

Previous Article ፍርድ ቤቱ የዲጂታል የሀብት ማስመዝገብ መርሐ-ግብር አስጀመረ
Next Article በፌደራል ፍርድ ቤቶች የተገልጋዮች የእርካታ ደረጃ በአማካይ 78 በመቶ መሆኑን ጥናት አመለከተ
Print
71