ፍርድ ቤቱ የዲጂታል የሀብት ማስመዝገብ መርሐ-ግብር አስጀመረ
/ Categories: News

ፍርድ ቤቱ የዲጂታል የሀብት ማስመዝገብ መርሐ-ግብር አስጀመረ

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የዲጂታል የሀብት ምዝገባና ማሳወቅ መርሐ-ግብር በፌደራል ፍርድ ቤቶች መጀመሩን መጋቢት 8 ቀን 2014 ዓ/ም በፍርድ ቤቱ የስብሰባ አዳራሽ በተካሔደ ሥነሥርዓት ይፋ አደረጉ፡፡

በፌደራል ፍርድ ቤቶች የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ተግባራዊ የሚደረገውን የዲጂታል የሀብት ምዝገባና ማሳወቅ መርሐ-ግብር የተጀመረው ፍርድ ቤቱ እና የፌደራል የሥነምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በጋራ ባዘጋጁት ሥነሥርዓት ላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ በተከናወነ ሥነሥርዓት ነው፡፡

በሀብት ምዝገባ ማስጀመሪያ ሥነሥርዓቱ ላይ የፌደራል የሥነምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ክቡር አቶ ወዶ አጦ ባስተላለፉት መልዕክት የኮሚሽን መስራያ ቤቱ ከዚህ በፊት የሃብት ምዝገባና ማሳወቅ ስራን በወረቀት ሲያከናወን የቆየ መሆኑን ጠቅሰው ከአሁን በኋላ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ባለማው ዲጂታል ስርዓት ምዝገባውን እንደሚስፈጽም ገልጸዋል፡፡   ከዲጂታል የሀብት ማስመዝገብ አሰራር በርካታ ጥቅሞች መካከል ስራና አሰራርን ማቀላጠፍ፣ ሚስጥር ጠባቂነት፣ የስራ ጫናን መቀነስ እና ግልጽነትና ተጠያቂነት ስርዓት ተጠቃሽ መሆናቸዉን ጠቁመዋል፡፡

በአዋጁ መሰረት ሃብት ማስመዝገብና ማሳወቅ ግዴታ የተጣለባቸው የፍርድ ቤቱ አመራሮችና በተለያዩ የአመራር እርከን ላይ የሚገኙ ሹመኞች እና ሰራተኞች የዲጂታል ዘዴውን ተጠቅመው ሃብታቸውን እንዲያስመዘግቡና እንዲያሳውቁ የጠቅላይ ፍርድ ቤት የማስፈጸም ሃላፊነት እንዲወስድና ለተግባራዊነቱም ተገቢውን ክትትል እንዲያደርግ ምክትል ኮሚሽነር ክቡር አቶ ወዶ አጦ ጠይቀዋል፡፡     

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በሥነሥርዓቱ ላይ በዲጂታል ዘዴ ሀብታቸዉን ባስመዘገቡበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ሙስናን በመከላከል ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ችግሩን መቀነስ እንደሚያስችል ያላቸውን እምነት ገልጸው ይህንም ከግብ ለማድረስ በህፃናት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት፤ ለመላው ማህበረሰብ የባህሪ ለውጥ ሊያመጣ የሚያስችል ግንዛቤ ማስጨበጥ፤  የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ማዋልና አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን እንዲሁም ተቋም መገንባት የኮሚሽኑ ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባው አስረድተዋል፡፡

ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አክለውም የዲጂታል የሀብት ምዝገባና ማሳወቅ ስርዓት ከግልፅነትና ወጪ ቆጠቢነት አንፃር ጥቅሙ የጎላ መሆኑን ጠቅሰዉ፣ ሙስናን ከመከላከያ መንገዶች አንዱ ወደ ኃላፊነት የሚመጡ ግለሰቦችን የኋላ ታሪክ በአግባቡ በማጥናት የሥነምግባር ደረጃቸውን በማረጋገጥ ለኃላፊነት እንዲታጩ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በፌደራል ፍርድ ቤቶች ቀልጣፋ አገልግሎትን ለማረጋገጥና ለሙስናና ብልሹ አሠራር ቀዳዳ የሚከፍቱ አሠራሮችን ለመዝጋት የባለጉዳዮች አገልግሎት አሰጣጥ ማንዋል በማዘጋጀት በአንድ መስኮት አገልግሎት ለማስተናገድ የሚያስችል ጅምር አሠራር ተግባራዊ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ በፍርድ ቤቶች መካከል የሚኖርን የመዝገብ ዝውውር ለማስቀረትም በፌደራል ፍርድ ቤቶች መካከል የዋይድ ኤርያ ኔትወርክ ዝርጋታ ለማስጀመር እንቅስቀሴ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከፍተኛ አመራሮች የተጀመረው የዲጂታል የሀብት ምዝገባም በሶስቱም ፍርድ ቤቶች በሚገኙ የሥራ ኃፊዎችና ሠራተኞች ደረጃ በደረጃ ተፈጻሚ እንደሚሆን አረጋግጠዋል፡፡

ከቡር አቶ ሰለሞን አረዳ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዝደንት በበኩላቸው የዲጂታል የሃብት ማስመዝገብና ማሳወቅ መርሃ ግብር በቀዳሚነት በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ውስጥ ተግባራዊ መደረጉ ከሙስና ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤት በሚቀርቡ ጉዳዮች ላይ ዳኝነት የሚሰጥ ተቋም እንደመሆኑ መጠን በመከላከሉ ዘርፍ የፍደርድ ቤት አመራሮች፣ ዳኞች ባለሙያዎች የአርዓያነት ሚናቸውን መውሰዳቸው ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

በህጋዊ መንገድ የተገኘ ሐብትን ማስመዝገብ ግልጽነትና ተጠያቂነት በመፍጠር ረገድ ትልድ ድርሻ ቢኖረውም ለተመዘገበው ሃብት ዋስትና የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡    

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት  

 

Previous Article የፍ/ቤቱ ዳኞች በጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር እና በመዛግብት አፈጻጸም ዙሪያ አበረታች ውጤት ማስመዝገባቸው ተገለጸ
Next Article ፍርድ ቤቱ የዩኒቨርሲቲ የሕግ ተማሪዎችን አቅም ለማጎልበት የሚያከናውነው ሥራ ትውልድን የማነጽ ተግባር እንደሆነ ተጠቆመ
Print
70