ፍርድ ቤቶች በዘጠኝ ወሩ ከአንድ መቶ 19 ሺህ በላይ ለሆኑ መዛግብት እልባት ሰጡ
/ Categories: News

ፍርድ ቤቶች በዘጠኝ ወሩ ከአንድ መቶ 19 ሺህ በላይ ለሆኑ መዛግብት እልባት ሰጡ

የፌደራል ፍርድ ቤቶች በ2013 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ለ119, 413 መዛግብት እልባት መስጠታቸውን የሶስቱ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የተጠቃለለ የዘጠኝ ወር የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አመለከተ፡፡

በሪፖርቱ መሠረት በሶስቱም ፍርድ ቤቶች በበጀት ዓመቱ ዕልባት እንዲያገኙ ከተያዙ መዛግብት በዘጠኝ ወሩ 118,417 መዛግብት ዕልባት እንዲያገኙ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም 119,413 መዛግብት ዕልባት በማግኘታቸው አፈጻጸማቸው 100.84% መድረሱን ለመረዳት ተችሏል፡፡

ይህ አፈጻጸም በዘጠኝ ወሩ ለየፍርድ ቤቶች ተይዘው ከነበሩ ዕቅዶች አንጻር ሲታይ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለ11,648 መዛግብት እልባት ለመስጠት ታቅዶ 10,238 መዛግብት ዕልባት በማግኘታቸው አፈጻጸሙ 87.89% ሲሆን በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለ19,777 መዛግብት እልባት ለመስጠት ታቅዶ 19,172 መዛግብት ዕልባት በማግኘታቸው አፈጻጸሙ 96.94% ደርሷል፡፡ በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ደግሞ ለ86,992 መዛግብት እልባት ለመስጠት ዕቅድ ተይዞ ለ90,003 መዛግብት ዕልባት በመሰጠቱ አፈጻጸሙ 103.46% የደረሰ መሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በሶስቱም ፍርድ ቤቶች ካለፈው በጀት ዓመት የተዛወሩ መዛግብትን ጨምሮ በአጠቃላይ 162,615 መዛግብት የቀረቡ ሲሆን የዘጠኝ ወሩ አፈጻጸሙ 74% መሆኑንም ሪፖርቱ ጨምሮ ጠቁሟል፡፡ ይህ አፈጻጸም የፍርድ ቤቶችን የማጥራት አቅም 97.91%፣ የመጨናነቅ ሁኔታ 1.36 እና የክምችት ምጣኔ 0.36 አድርሶታል፡፡

ባለፈው በጀት ዓመት የCOVID-19 ወረርሽኝ ስርጭት ለመቀነስና ለመግታት ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ እንዲሆኑ በመደረጋቸው የተከማቹ፣ አዲስ እና እንደገና ተከፍተው ለፍርድ ቤቶች የቀረቡ አቤቱታዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን መጨመሩ በዚህ በጀት ዓመት ለእልባት የቀረቡ መዛግብት መጠን ከፍ እንዲል ምክንያት ነው ተብሏል፡፡

ፌ/ጠ/ፍ/ቤት የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article ፍርድ ቤቱ በአገልግሎት አሰጣጥ መልካም ተሞክሮ ለመቅሰም የመስክ ጉብኝት አደረገ
Next Article ለስትራቴጂካዊ ዕቅድ ዝግጅት የተካሄዱ የትንተና ጥናቶች ላይ ዓብይና የቴክኒክ ኮሚቴ ተጨማሪ ግብአት ሰጡ
Print
351