«ትልቁ የመሪዎች መለያ አውቃለሁ ባይነት ሳይሆን ለመማር ዝግጁ መሆን ነው»
/ Categories: News

«ትልቁ የመሪዎች መለያ አውቃለሁ ባይነት ሳይሆን ለመማር ዝግጁ መሆን ነው»

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ክብርት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ

ክብርት ፕሬዚደንትዋ ይህን የገለጹት የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዚደንትና የፌደራል ፍርድ ቤቶች ቃል አቀባይ የሆኑት ክቡር አቶ ተስፋዬ ንዋይ «የአመራር ክህሎት» በሚል ርዕስ ያሳተሙትን መጽሐፍ ሐምሌ 2 ቀን 2014 ዓ.ም በሐያት ሪጀንሲ ሆቴል ለማስመረቅና ለማስገምገም በተዘጋጀ ሥነሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡

በመጽሐፉ የማስመረቂያና የማስገምገሚያ ሥነሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር መሪዎች የዕድሜ ልክ ተማሪዎች ናቸው፣ ያማክራሉ፣ ያሳትፋሉ፣ ውሳኔ የሚሰጡት ብዙ ከተረዱ በኋላ ነው ያሉ ሲሆን መሪዎች ብዙ ጊዜ የሚደርሱበት ውሳኔ በስምምነት ላይ የተመሠረተ ነው፤ በስምምነት ላይ የተደረሰ ውሳኔ የበለጠ የተፈጻሚነት ዕድል እንዳለውም ይገነዘባሉ ብለዋል፡፡

መሪዎች በሁኔታዎች ይፈጠራሉ የሚል እምነት እንዳላቸው የገለጹት ክብርት ፕሬዚደንትዋ፣ መሪዎች ሌላው ሰው የማይታየው ነገር እንደሚታያቸውና አንዳንድ የመሪነት ክህሎቶች እንደሚያስፈልጓቸውም አስረድተዋል፡፡

ቀላል ከሚመስሉ ነገር ግን ሌሎች ውስብስብ የመሪ ዲሲፒሊኖችን ለማዳበር ከሚያግዙ ባህሪዎች መካከል በቀጠሮ ቦታ በሰዓት መገኘት፣ ቸኩሎ ከመናገር አስቦ መናገር፣ የሚወስዱ እርምጃዎችም ሆኑ ጥቅም ላይ የሚውሉ ቃላት እንድምታ እንዳላቸው መገንዘብ፣ ፀባያችን ተለዋዋጭ ሳይሆን ተገማች መሆን፣ ውጫዊ በሆነ ሁኔታ አለመናጋት፣ የማዳመጥ ችሎታ እና የመሳሰሉት ጠቃሚ ልምዶች ናቸው ብለዋል፡፡

ሌላውና ብዙውን ጊዜ ሰዎችን የሚያስቸግረው ቀና ያልሆነ አስተሳሰብ ነው ያሉት ክብርት ፕሬዚደንትዋ፣ ቀና ያልሆነ አስተሳሰብ ምንጩ ሌላውን ጥፋተኛ ማድረግ ነው በማለት ይህም ውጤታማነትን እንደሚያቀጭጭና ግንኙነትንም እንደሚያበላሽ አስምረውበታል፡፡

የዚህ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ጠንካራ መሪ ለመሆን እንደሚቸገሩ በመጥቀስ ከዚህ አይነት የአእምሮ ምልልስ ቀለበት ለመውጣት ከሚረዱ ዘዴዎችም መካከል ዋናው ነገር ወደውስጥ መመልከትና ችግሩ እንዳለብን እራሳችንን ማሳመን ነው በማለት «ቀና ያልሆነ ልቦና ቂመኝነት ይከተለዋል፣ ይቅርታ ለመስጠትም በጣም ይከብደዋል» ብለዋል፡፡

መሪዎች ሀሳባቸውን በደንብ ይገልጻሉ፤ የሚሠሩትን ሥራ ብቻ ሳይሆን አንድን ሥራ ለምን እንደሚሰሩ ማስረዳትም ይጠበቅባቸዋል በማለት ገልጸዋል፡፡

ስለመሪነት እጅግ በርካታ መጽሐፍት የተጻፉ መሆኑን ጠቅሰው የመጽሐፉ ደራሲ ክቡር አቶ ተስፋዬም ንዋይም በርካታ የመሪና የአመራር ምሳሌዎችን በመጽሐፋቸው አጋርተውናል ብለዋል፡፡

«የአመራር ክህሎት» በሚል ርዕስ የተዘጋጀው መጽሐፍ ስለመሪ ምንነት፣ስለተቋማዊ ባህል፣ ስለመሪነት ክህሎቶች እና ብቃቶች፣ በሀገራችን ስላሉ የአመራር ችግሮች እና መፍትሔዎች የተዳሰሱበት የሕትመት ውጤት ነው፡፡

ሁለት ክፍሎችንና እያንዳንዱ ክፍል አራት ምዕራፎችን በማካተት በ313 ገጾች በተዘጋጀው መጽሐፍ ላይ ያላቸውን እይታ የኮተቤ ትምሕርት  ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ረዳት ፕሮፌሰር ብርሐነ መስቀል ጠና እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ም/ ዋና ኮሚሽነር ክብርት ራኬብ መሰለ በመድረኩ ላይ ያቀረቡ ሲሆን ይህን ተከትሎ ከመድረኩ ተሳታፊዎች የተለያዩ አስተያየቶች ቀርበው በቀረቡት አስተያየቶች ላይም ውይይት ተደርጓል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ሆነ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የሰጠው አንድም የዳኝነት ሹመት የለም
Next Article ዜና መግለጫ
Print
119