Sunday, February 13, 2022 / Categories: News «የፌደራል ፍርድ ቤቶች አሁናዊ ሁኔታ እና የወደፊት ዕይታ» በሚል ርዕስ የተዘጋጀ መድረክ ተካሔደ «የፌደራል ፍርድ ቤቶች አሁናዊ ሁኔታ እና የወደፊት ዕይታ» በሚል ርዕስ የተዘጋጀ መድረክ ተካሔደ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ «የፌደራል ፍርድ ቤቶች አሁናዊ ሁኔታ እና የወደፊት ዕይታ /State of the Judiciary/» በሚል ርዕስ ለሁለተኛ ጊዜ የተዘጋጀ ጉባዔ በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ የካቲት 6 ቀን 2014 ዓ.ም ተካሔደ፡፡ የመጀመሪያው ጉባዔ በ2012 የተካሔደ ሲሆን መድረኩ በኮቪድ 19 ምክንያት ተቋርጦ ከቆየ በኋላ ሁለተኛው ጉባዔ በፌደራል ፍርድ ቤቶች በ2013 በጀት ዓመት እና በ2014 ግማሽ በጀት ዓመት በተገኙ ዋና ዋና ውጤቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ተከናውኗል፡፡ መድረኩ በፌደራል የዳኝነት ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት፣ የተገኙ ውጤቶች፣ ያጋጠሙ ችግሮችና የወደፊት የትኩረት መስኮችን የሚዳስስ ሪፖርት ለሕዝቡ፣ ለባለድርሻ አካላትና ለከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም ለልማት አጋሮች የሚገለጽበት ሁነት ነው፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ በጉባዔው መክፈቻ ላይ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ይህን ዓይነት ጉባዔ በዓመት አንድ ጊዜ ማከናወን በአሜሪካ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አውስትራሊያ እና በሌሎችም አገሮች የተለመደ ትልቅ አገራዊ ክንውን መሆኑን ገልጸው በአገራችንም በየዓመቱ እንዲከናወን ዕቅድ ተይዞለት በመተግበር ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ አገራቱ በጉባዔዎቻቸው ሶስተኛው የመንግሥት አካል የሆነው ፍርድ ቤት በዓመት ውስጥ ያከናወናቸውን ተግባራት፣ የወደፊት ስትራቴጅያቸውንና ያጋጠሟቸውን ችግሮች ለም/ቤት አባላት፣ ለአስፈጻሚው አካል ለሕግ ማሕበረሰቡ፣ መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት፣ ለሌሎች ባለድርሻ አካላትና ለሕዝብ በማቅረብ የተሻለ የዳኝነት ተቋም አብሮ ለመገንባት ጥሪ የሚያቀርቡበት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በበኩላቸው በጉባኤው ላይ በ2013 በጀት ዓመት እና በ2014 ግማሽ በጀት ዓመት በፌደራል ፍርድ ቤቶች በተከናወኑ ዋና ዋና ውጤቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ሪፖርት ለተሳታፊዎች አቅርበዋል፡፡ ክብርት ፕሬዚደንትዋ እንደገለጹት አዲሱ የፍርድ ቤቱ አመራር ወደሥራ ሲገባ በፌደራል ፍርድ ቤቶች በርካታ የአሠራር ማነቆዎች ያጋጠማቸው መሆኑን አስታውሰው ከእነዚህ መካከል ቀዳሚ ጉዳዮችን ለይተው በፍ/ቤቱ የተፋጠነ፣ ጥራት ያለው፣ ተደራሽነትን ያማከለ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላሉ ተብለው ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች በሶስት ዋና ዋና ርዕሶች ስር በመመደብ ለተግባራዊነቱ እንቅስቃሴ ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ እነዚህ የትኩረት መስኮችም የዳኝነት ነጻነት፣ ገለልተኝነት እና ተጠያቂነትን ለማጠናከር፤ የዳኝነት አገልግሎት ጥራት እና ቅልጥፍናን ለማሻሻል እንዲሁም የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ የተሰሩ ተግባራት መሆናቸውን ጠቅሰው በዚህ ዙሪያ የተከናወኑ ተግባራትንም በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ በመድረኩ ላይ በፌደራል ፍርድ ቤቶች ከ2014-2018 ዓ.ም ለአምስት ዓመታት ተግባራዊ እንዲሆን የተዘጋጀ ስትራቴጅያዊ ዕቅድን የተመለከተ ማብራሪያ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዚደንት እና የፌደራል ፍርድ ቤቶች ቃል አቀባይ በሆኑት በክቡር አቶ ተስፋዬ ንዋይ ቀርቧል፡፡ በተመሳሳይም ሕብረተሰቡ ስለፍርድ ቤቶች ያለውን አመለካከት በተመለከተ የተካሔደ የጥናት ውጤት «አብከን» በተሰኘ አማካሪ ድርጅት ቀርቦ በተሳታፊዎቹ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በጉባኤው ላይ ሚኒስትሮች፣ የተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ኃላፊዎች፣ የፌደራል እና የክልል ፍርድ ቤቶች አመራሮች ዳኞች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡ ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በጉባዔው ላይ ያቀረቡት ሙሉ ሪፖርት በዚህ መስፈንጠሪያ ያገኑታል፡፡ https://www.fsc.gov.et/Digital-Law-Library/State-of-the-Judiciary/%e1%8b%a8%e1%8d%8c%e1%8b%b4%e1%88%ab%e1%88%8d-%e1%8b%b3%e1%8a%9d%e1%8a%90%e1%89%b5-%e1%8a%a0%e1%88%81%e1%8a%93%e1%8b%8a-%e1%88%81%e1%8a%94%e1%89%b3%e1%8a%93-%e1%8b%a8%e1%8b%88%e1%8b%b0%e1%8d%8a%e1%89%b5-%e1%8b%95%e1%8b%ad%e1%89%b3-%e1%8b%a8%e1%8a%ab%e1%89%b2%e1%89%b5-2014-%e1%88%aa%e1%8d%96%e1%88%ad%e1%89%b5-the-state-of-the-judiciary-february-2022-report-1 ነጻና ገለልተኛ ፍርድ ቤት ለህግ የበላይነት የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት Previous Article የቅድመ መዋቅር ነባራዊ ሁኔታ ትንተና እና ረቂቅ ተቋማዊ ለዕላዊ መዋቅር ላይ ውይይት ተካሄደ Next Article የፌደራል ፍርድ ቤቶችን የዳኝነት ነጻነት፣ ገለልተኝነት እና ተጠያቂነትን ለማጠናከር የተወሰዱ እርምጃዎች Print 2175