በፍርድ ቤቱ የፍትሐብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው
/ Categories: News

በፍርድ ቤቱ የፍትሐብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው

በቅርቡ የፀደቀውን የፌደራል ፍርድ ቤቶች የፍትሐብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ በ2014 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊው ቅድመ-ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

የፌደራል ፍርድ ቤቶች የፍትሐብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 008/2013ን ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ለማስተዋወቅና ትግበራውን ለማስጀመር ነሐሴ 8 ቀን 2012 ዓ.ም በራዲሰን ብሉ ሆቴል ውይይት ተካሒዷል፡፡

በመድረኩ ላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ በጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር ጽንሰ-ሐሳብና መሠረታዊ መርሆዎች እንዲሁም በጸደቀው የፌደራል ፍርድ ቤቶች የፍትሐብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 008/2013 ላይ ለፍ/ቤቱ ዳኞች ገለጻ አድርገዋል፡፡

ክቡር ም/ፕሬዚደንቱ በገለጻቸው በደንቡ ይዘት ላይ በተለይም በጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር ዓላማና ግብ፣ ስለግልጽ ችሎት እና ቀዳሚነት (በዳኝነት ቅድሚያ ስለሚሰጣቸው ጉዳዮች)፣ ስለቀጠሮ ፖሊሲ፣ በጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር የተለያዩ አካላት ስላላቸው ተግባርና ኃላፊነት እንዲሁም የጉዳዮች እልባት የመስጫ የጊዜ ገደብ ላይ ሰፊ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡

የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ ከዳኞች በተጨማሪ የሪጅስትራሮች፣ የአስተዳደር ሠራተኞች፣ የጠበቆች እና የሌሎች ባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ እንደሚሆንና ለዚህም በየደረጃው አስፈላጊው ሥልጠና እንደሚሰጥ በመድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡

በመመሪያው የአተገባበር ሒደትም የዳኞች የቁጥጥርና ክትትል ሚና መተኪያ የሌለው ስለመሆኑም ተነስቷል፡፡

የመመሪያው ዓላማ የሥነሥርዓት ሕጎችን በአተገባበር ረገድ የተሟላ በማድረግ ለፍርድ ቤቶች የሚቀርቡ ጉዳዮች የተፋጠነ እና ጥራት ያለው ዳኝነት መስጠት የሚያስችል አሠራር መፍጠር ነው ተብሏል፡፡

መመሪያው ተግባራዊ ሲሆን የጉዳዮች ሒደትና እልባት መስጫ ጊዜ መጓተትን በማስቀረት ዜጎች በዳኝነት ሥርዓቱ ላይ ያላቸው አመኔታና እርካታ እንዲጨምር ለማድረግ እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡

በተጨማሪም ለጉዳዮች እንደየመደባቸውና ተናጠል ባህሪያቸው ተመጣጣኝ የሆነ ትኩረት ለመስጠት፣ ለሁሉም ተከራካሪ ወገኖች የጉዳዮች ሒደትና እልባት መስጫ ጊዜን ተገማች የማድረግና በጉዳዮች ሂደት ውስጥ የሚከናወኑ ድርጊቶችን ጥራት የመጨመር ፋይዳ እንደሚኖረው ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

የቀረበውን ማብራሪያ ተከትሎ ከተሳታፊዎች በርካታ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበው ከመድረክ ምላሽ የተሰጠባቸው ሲሆን ክቡር አቶ ሰለሞን አረዳ በማጠቃለያ መልዕክታቸው መመሪያው ተጠያቂነትን የሚያስከትል ሳይሆን ዳኞች ሃላፊነታችሁን እንድትወጡ የሚያግዝ  ነው በለዋል፡፡  በጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኞችና ሠራተኞች አሁናዊ አቋም የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደርን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያበረታታ መሆኑንም ተጠቅሷል፡፡

ክብርት ወ/ሮ መዓዛ በበኩላቸው ለመመሪያው መተግበር በጠቅላይ ፍርድ ቤት የመዛግብት ፍሰትን ከዳኞች ቁጥር ጋር ለማመጣጠን በማሰብ የዳኞችን ቁጥር መጨመር መፍትሔ አይሆንም ካሉ በኋላ አሰራራችንን በመፈተሸ የጎደለንን ነገር ለመሙላት መስራት ይጠበቅብናል፡፡  እንደ ሌሎች የተሻለ ልምድ እንደኣላቸው ሃገራት ጠቅላይ ፍርድ ቤትን እንደስሙ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለማድረግ እያሰብን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡    

በፍርድ ቤቱ አሠራር ላይ ጉልህ ትራንስፎርሜሽን እንደሚያመጣ እናምናለን ያሉት አስተያየት ሰጭዎቹ፣ ጽንሰ-ሐሳቡ በሌሎች አገሮች በሚገኙ የትምሕርት ተቋማት እንደሚደረገው ሁሉ በአገራችን ዩኒቨርሲቲዎች በሚገኙ የሕግ ትምሕርት ቤቶች እንደአንድ የትምሕርት ዓይነት ቢሰጥ መልካም እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Previous Article በፍ/ቤቶች የዳኝነት ነጻነትን፣ ገለልተኝነትን እና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተገለጸ
Next Article የፌደራል ዳኞች የሥነምግባር እና የዲሲፒሊን ክስ ሥነሥርዓት ደንብ ዓለም አቀፋዊ የዳኝነት መርሆዎችን መሠረት በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ
Print
174