የዓለምአቀፍ የ16 ቀን ፀረ-ጾታዊ ጥቃት እንቅስቃሴ ለማስጀመር የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባዘጋጀው መድረክ በክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ የተላለፈ መልዕክት
/ Categories: News

የዓለምአቀፍ የ16 ቀን ፀረ-ጾታዊ ጥቃት እንቅስቃሴ ለማስጀመር የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባዘጋጀው መድረክ በክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ የተላለፈ መልዕክት

በዚህ ዓመት በሴቶች ጥቃት ዙሪያ ስንነጋገር በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተከሰተው ጦርነት ምክንያት እጅግ አስደንጋጭ፣ የሴቶችን ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆችን ሰብዓዊ ክብር የሚያዋርዱ ጥቃቶች የተፈጸሙ መሆናቸው ሪፖርት በመደረግ ላይ ነው፡፡ እንዲህ ያሉት ጉዳዮች አስቸኳይ ሰብዓዊ እና የፍትህ ምላሽ ማግኘት ይገባቸዋል፡፡

እንደ COVID-19 እና ጦርነት ያሉ ችግሮች ሲከሰቱ በአጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች፣ በተለይም የሴቶች መብቶች ጥሰት የመስፋፋቱ ሁኔታ የማይቀር በመሆኑ ሁኔታው ልዩ ትኩረትና ልዩ ርብርብ የሚጠይቅ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ለተጠቂ ሴቶች ማገገሚያ ልዩ Fund ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው፡፡ በግጭቶች የተጎዱት የሕብረተሰብ ክፍሎች ለማገገም እንዲችሉ እና ሕብረተሰቡ በሂደት ወደ መደበኛ ሕይወት መመለስ እንዲችል ከመደበኛ የፍትሕ ሥርዓቶች በተጓዳኝ አማራጭ የፍትሕ እርምጃዎች አስፈላጊ ናቸው፡፡

የፌደራል ፍርድ ቤቶች ሚና አስመልክቶ በሴቶች እና በሕጻናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን በተመለከተ የሚቀርቡ ጉዳዮችን የሚያስተናግዱበት 8 ችሎቶች በ10 ክፍለ ከተሞች ተደራጅተዋል፡፡ የዳኝነት ሂደቱ ሚዛናዊነቱን የጠበቀ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በሴቶች እና በሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ባህርይ ባገናዘበ መልኩ ፍትሐዊ ውሳኔ እንዲገኝ የተለያዩ ሥልጠናዎች እየተሠጡ እና የአሠራር መመሪያዎች እየተዘጋጁ ይገኛል፡፡

ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በዝግጅት ላይ ያለው የሴቶች እና የሕጻናት ችሎት የአሠራር መመሪያ "Bench Book" ዳኞች ሕግ የመተርጎም ኃላፊነታቸውን ሲወጡ በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ያሉትን መልካም ተሞክሮችን ከግምት በማስገባት በሴቶች ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አድሎ የሚፈጥሩ ሕጎች እና አሠራሮችን የመለየት ክህሎት ለማዳበር የሚያግዝ ነው፡፡

በ2013 ዓ.ም 1,244 ያህል ጉዳዮች በሴቶች እና ሕፃናት ችሎት ታይተው 644 የሚሆኑት ጉዳዮች እልባት አግኝተዋል፡፡ በሴቶችና በሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ቁጥር ከተገለፀው ቁጥር በእጅጉ ሊሰፋ እንደሚችል ነገር ግን ጉዳዩቹ በተለያየ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫናዎች ምክንያት እንዲሁም የጥቃት ተጋላጮች መብታቸውን ባለማወቅ እና የፍትሕ ተደራሽነት ስጋት ምክንያት ወደ አደባባይ ያለመምጣት እድላቸው ሰፊ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ባለድርሻዎች ቀጣይ ሥራዎችን በትጋት እንዲሰሩ ጥሪ ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡

ምንጭ፡- ፌ/ጠ/ፍ/ቤት ፕሬዝደንት ጽ/ቤት

Previous Article ዳኞች ስራ ላይ ባሉ ህጎችና ፋይዳቸው ላይ የጽሁፍ ውጤቶችን ማበርከት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ
Next Article በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በተለያየ መደብና ስራ ክፍሎች ሲከናወን የነበረውን የሬጅስትራር አገልግሎት ወደ አንድ ማዕከል ሰብሰብ በማድረግ ባለሙያዎች እና ሰራተኞች በቡድን እና በትብብር መርህ ስራቸውን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ
Print
90