Monday, May 25, 2026 / Categories: News ለሶሻል ወርክ ባለሞያዎች በተዘጋጀ የስልጠና ማንዋል ረቂቅ ላይ የቫሊዴሽን ወርክ ሾፕ ተካሄደ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የህፃናት ፍትህ ፕሮጀክት ዳይሬክቶሬት በፍትህ ስርዓት ውስጥ የሚያገለግሉ የማህበራዊ ሳይንስ ባለሞያዎችን ሚና ለማጎልበት የሚያግዝ የስልጠና ማንዋል የመጨረሻ ረቂቅ ሰነድ ላይ የውይይት እና የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ተካሂዷል፡፡ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ድሪባ ፈዬራ በመድረኩ መክፈቻ ላይ ህጻናት በፍትህ ስርዓት ውስጥ ሲያልፉ ተጎጂ የሚሆኑበትን አጋጣሚ በዘላቂነት ለመቅረፍ በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ ለሚያገለግሉ የሶሻል ወርክ ባለሞያዎች የስልጠና ማኑዋል መዘጋጀቱ አስፈላጊ መሆኑንና በከፍተኛ አመራሩ አቅጣጫ ተሰጥቶበት የተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል። የህጻናት ፍትህ ፕሮጀክት ዳይሬክቶሬት በማዋቀር ለህጻናት ተስማሚ የችሎት ማስቻያ ቦታ እንዲኖር፣ ችሎቶች በቴክኖሎጂ እንዲደራጁ፣ የአሰራር ስርዓትን በመዘርጋት በተደራጀ የሰው ኃይል እንዲመራ ማድረግ እና መመሪያና ማንዋሎችን በማዘጋጀት በሁሉም ፍርድ ቤቶች ወጥነት ያለው የፍትህ አገልግሎት እንዲኖር በማድረግ ሰፊ ስራ መሰራቱን አያይዘው ተናግረዋል። የስልጠና ማንዋሉ የመጨረሻ ረቂቅ ላይ ከመጀመሪያው ረቂቅ ጀምሮ የተሰበሰቡ ግብዓቶችንና አስተያየቶችን በማካተት 11 ሞጁሎችን የያዘ ሰነድ መዘጋጀቱ ታውቋል። በቀረበው የስልጠና ማንዋል ላይ ከተሳታፊዎች ሃሳብ አስተያየቶች ተነስተው ውይይቶች ተካሂዷል። ይህ የስልጠና ማንዋል በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በተባበሩት መንግስታት የህዝብ ፈንድ (UNFPA) በጋራ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በመድረኩ ላይ ከፌደራል ፍርድ ቤቶች የተውጣጡ ዳኞች እና የሶሻል ወርክ ባለሙያዎች እንዲሁም ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣ ከፍትህ ሚኒስቴር እና ከአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ቢሮ ተሳትፈዋል። Previous Article የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከፍተኛ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተከናወኑ የሪፎርም እና የዲጂታላይዜሽን ሥራዎችን ጎበኙ Next Article ዘመናዊ የህጻናት ማስመስከሪያ ክፍል የስራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሄደ Print 413