በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እየተሰሩ ያሉ የለውጥ ስራዎችን በተመለከተ ለተቋሙ የቀድሞ አመራሮች ገለጻ ተደረገ
/ Categories: News

በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እየተሰሩ ያሉ የለውጥ ስራዎችን በተመለከተ ለተቋሙ የቀድሞ አመራሮች ገለጻ ተደረገ

በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፕሬዝዳንትነትና ምክትል ፕሬዝዳንትነት ሲያገለግሉ የነበሩ የቀድሞ አመራሮች በፍርድ ቤቱ ተገኝተው አሁን ላይ እየተሰሩ ያሉ ዋና ዋና የለውጥ ስራዎችን በተመለከተ ውይይትና ምልከታ አድርገዋል።

‎‎ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት፤ የተቋም ግንባታ የቅብብሎሽ ውጤት መሆኑን አንስተው፣ ይህ መድረክ ከዚህ በፊት ተጀምረው የተጠናቀቁ የስራ ክንውኖችን ለማሳየት እንዲሁም አሁን በያዝነው የሪፎርም ስራ እየተከናወኑ ያሉ ዋና ዋና የሪፎርም ተግባራትን ለማስተዋወቅ ያለመ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

‎‎ቀጣይ ግንኙነቶችን በማጠናከር በጋራ የዳኝነት ዘርፉን የበለጠ የተሻለ በማድረግ አገር በምትፈልገው ልክ ለመስራት እንዲቻል መሰል ግንኙነቶች አስፈላጊ መሆናቸው ታምኖበት የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን ክቡር ፕሬዝዳንቱ አያይዘው ገልጸዋል።

‎‎በገለጻው ፍርድ ቤቱ እያከናወናቸው ያሉ አበይት የለውጥ ስራዎች በተለይም የዳኝነት ነጻነት እና ተጠያቂነት ከማጠናከር፣ የዳኝነት አገልግሎት ጥራት ከማረጋገጥ፣ ቅልጥፍና እና ውጤታማነትን ከማሳደግ፣ ግልጽነትን ከማረጋገጥ፣ የላቀ እና ውጤታማ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከማሳደግ፤ ከሀገራዊ እና አህጉራዊ እንዲሁም አለም አቀፋዊ ትብብር ከማጠናከር አንጻር የተሰሩ የሪፎርም ተግባራትና የተገኙት ውጤቶች በተመለከተ ለቀድሞ አመራሮች ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

‎‎እንደዚህ አይነት መድረኮችና ግንኙነቶች የባለቤትነት ስሜትን የሚፈጥሩ መሆናቸውን በመጥቀስ ይህንን ላመቻቹት የተቋሙ አመራሮች ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፤ በፍርድ ቤቱ እየተሰሩ ያሉ የሪፎርም ስራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን ለቀጣይነታቸውም የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን በውይይቱ ወቅት አንስተዋል።

‎‎የቀድሞ አመራሮች የሪፎርም ስራዎችን በአካል ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን፤ ዘመኑ የሚፈቅደውን አሰራር ለመከተል የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ መታዘባቸውን ገልጸዋል።

‎ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገባ የዳኝነት ስራን ምቹ እና ቀልጣፋ ለማድረግ ያግዛል ተብሎ የሚጠበቀው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አዲሱ ህንጻን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። የህንጻ ግንባታው ብዙ ችግሮችን ለማቃለል የሚያስችልና የዳኝነት ስራን በሚመችና በተቀላጠፈ መልኩ ለማከናወን የሚያግዝ፣ የሚሰሩ የሪፎርም ስራዎችን በይበልጥ ለመተግበር የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል።

Previous Article ዘመናዊ የህጻናት ማስመስከሪያ ክፍል የስራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሄደ
Next Article ለበጎ ፈቃደኛ ጠበቆችና የህግ አገልግሎት መስጫ ማዕከል አስተባበሪዎች የልምድ ልውውጥ መድረክ ተካሄደ
Print
408