የፌደራል ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ ሆነው ስለሚቆዩባቸው ጊዜያት የተሰጠ መግለጫ
/ Categories: News

የፌደራል ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ ሆነው ስለሚቆዩባቸው ጊዜያት የተሰጠ መግለጫ

በ2018 ዓ.ም በፌደራል ፍርድ ቤቶች በርካታ መልካም አፈጻጸሞች የተመዘገቡበት ዓመት ሆኖ ያለፈ ሲሆን ከመዝገብ አፈጻጸም አኳያ በዓመቱ ለ193,590 መዛግብት ዕልባት ለመስጠት በዕቅድ ተይዞ ለ190,065 መዛግብት ዕልባት በመስጠት የዓመቱ አፈጻጸም 98.2% ደርሷል።

‎ይህ አፈጻጸም ለፍርድ ቤቶች ተይዘው ከነበሩ ዕቅዶች አንጻር ሲታይ በጠቅላይ ፍርድ ቤት 19,898 መዛግብት ታቅደው 18,503 መዛግብት ዕልባት በማግኘታቸው አፈጻጸሙ 92.9%፤ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 26,206 መዛግብት ታቅደው 27,631 መዛግብት ዕልባት በማግኘታቸው አፈጻጸሙ 105.4%፤ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 147,486 መዛግብት ታቅደው ለ143,931 ዕልባት በመስጠት አፈጻጸሙ 97.6% ደርሷል።

‎‎የፌደራል ፍርድ ቤቶች በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀፅ 38 በተደነገገው መሠረት በየዓመቱ ከነሐሴ 1 ቀን እስከ መስከረም 30 ቀን ድረስ ዝግ እንደሚሆኑ ይገልጻል። በዚህም መሰረት ከነሐሴ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ የፌደራል ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ ሆነው ይቆያሉ።

‎‎የፌደራል ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ ሆነው በሚቆዩባቸው በእነዚህ ሁለት ወራት፣ በባህሪያቸው አስቸኳይ የሆኑና ጊዜ የማይሰጡ፣ በዜጎች መብትና በአገር ልማት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ አቤቱታዎች እንዲሁም ለውሳኔ የደረሱ መዛግብትን መርምሮ ውሳኔ የመስጠት አገልግሎቶች የሚቀጥሉ ይሆናል።

‎በወንጀል ጉዳዮች፤ ሕፃናት የያዙ ሴቶች እና በሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ የወጣት ጥፋተኞችን የሚመለከቱ የይግባኝ ጉዳዮች፣ ለወንጀል ምርመራ በሚቀርቡ የጊዜ ቀጠሮዎች፣ የዋስትና ትዕዛዝ ወይም ውሳኔ ላይ የሚቀርቡ የይግባኝ ክርክሮችና አቤቱታዎች፣ በወንጀል ሕግ አንቀፅ 201 እና በተከታዮቹ መሠረት የሚቀርቡ በአመክሮ መለቀቅ እንዲሁም በአንቀፅ 175 መሠረት መሰየምን በሚመለከት የሚቀርቡ አቤቱታዎች፣ የእግድ እና የመፈታት አቤቱታዎች እንዲሁም በችሎቱ አስቸኳይነታቸው የሚታመኑ መሰል ጉዳዮች፤

‎‎በፍትሐብሔር ጉዳዮች፤ የቀለብ እና ተያያዥነት ያላቸው የቤተሰብ ጉዳዮች አቤቱታዎች፣ አስቸኳይ መፍትሔ የሚፈልጉ የንግድ እና ሌሎች አቤቱታዎች፣ በግራ ቀኝ ወገኖች ስምምነት ወይም በአንድ ወገን የሚቀርብ ከመዝገብ ጋር ይያያዝልኝ አቤቱታዎች፣ በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ቁጥር 177 መሠረት የሚቀርቡ አካልን ነፃ የማውጣት አቤቱታዎች የሚስተናገዱ ይሆናል፡፡

‎‎የሰበር አጣሪ ችሎት በመደበኛ ጊዜ የሚያከናውነውን አጣርቶ ውሳኔ የመስጠት ሥራ ከነሐሴ 1 ቀን 2018 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የዳኝነት አገልግሎት መስጠቱን የሚቀጥል ሲሆን፤ የተረኛ ችሎት በጠቅላይ ፍርድ ቤት ከጳጉሜ 1 ቀን 2018 ዓ.ም እስከ መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም፤ በከፍተኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ደግሞ ከነሐሴ 1 ቀን 2018 ዓ.ም እስከ መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ ይከናወናል።

‎‎ከጥቅምት 1 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ ዳኞች በመደበኛ ችሎቶቻቸው ተገኝተው በክረምቱ የተሰጡ ውሳኔዎችን ለተከራካሪዎች ለመግለጽ የሚያዘጋጁበት ወቅት ሲሆን፣ አዳዲስ አቤቱታዎችና ጥያቄዎች በመደበኛ ችሎቶች መስተናገድ ይጀምራሉ። በክረምቱ የእረፍት ጊዜ ውሳኔ ያገኙ መዛግብት ከጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 6 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ በችሎት ለተከራካሪዎች ስለሚገለጹ ባለጉዳዮች በነዚህ ቀናት ቀርበው ውሳኔያቸውን እንዲወስዱ እስከ መስከረም 28 ቀን 2019 ዓ.ም ባሉት ቀናት በስልክ ወይም በአጭር የጽሑፍ መልእክት (SMS) ጥሪ ይደረግላቸዋል።

‎‎የ2018 ዓ.ም የሥራ ዘመን ካለፈው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር የተሻለ አፈጻጸም የተመዘገበበት ሲሆን፣ ከመዝገብ አፈጻፀም ባሻገር የዳኝነት ነፃነት፣ ገለልተኝነት፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነት የተጠናከረበት፣ የዳኝነት ቅልጥፍናንና የውሳኔ ጥራትን ማሳደግ፣ የአካላዊ ተደራሽነትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማጎልበት የተቻለበት ሆኖ አልፏል። በተለይም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በበጀት ዓመቱ የዳኝነት አገልግሎቱን ለማዘመንና ዲጂታላይዝ ለማድረግ ባደረገው ጥረት ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ በዚህም ችሎቶችን ስማርት የማድረግ እና የርቀት ዳኝነት የማጠናከር ሥራዎች ለዳኝነት ቅልጥፍና እና ተደራሽነት ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።

‎የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለተመዘገቡት መልካም አፈጻጸሞችና ስኬቶች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላደረጉ ክቡራን ዳኞች፣ ረዳት ዳኞች፣ ሬጅስትራሮች፣ የሥራ ኃላፊዎች፣ የአስተዳደር ሠራተኞች፣ እንዲሁም ድጋፍ ሲያደርጉ ለነበሩ አጋር ባለድርሻ አካላት በሙሉ በፍርድ ቤቱ ማኅበረሰብ ስም ላቅ ያለ ምስጋና ያቀርባል።

‎ለላቀ የዳኝነት አገልግሎት እንተጋለን!

‎የኢፌዴሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት

‎ሐምሌ 30 ቀን 2018 ዓ.ም

Previous Article በፌደራል ፍርድ ቤቶች ተጨማሪ ስማርት ችሎቶች አገልግሎት መስጠት ጀመሩ
Next Article አገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች መድረክ እየተካሄደ ይገኛል
Print
330