Monday, August 10, 2026 / Categories: News የፌደራል ፍርድ ቤቶች ጉባኤ ተካሄደ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ጉባኤ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትና የጉባኤው ሰብሳቢ ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በመክፈቻ ንግግራቸው፤ በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 መሠረት የተቋቋመው የፌደራል ጉባኤ የዳኝነት ነፃነትና ገለልተኝነትን የመጠበቅ፣ የአሰራር መመሪያዎችን የማውጣትና የማሻሻል እንዲሁም አገራዊ የዳኝነት ሂደቱን የማጠናከር ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል። ክቡር ፕሬዝዳንቱ አያይዘውም፤ የዳኝነት አገልግሎቱን ለተገልጋዮች ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግና የሕዝብን እንግልት እንዲሁም አላስፈላጊ ወጪ ለመቀነስ የሚያስችሉ አሰራሮችን በመዘርጋት መስራት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ጉባኤው በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የጋራ ግንዛቤ በመፍጠሩ ውጤታማ እንደነበር ተናግረዋል። በመድረኩ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ጉባኤ እና የዳኝነት ግንኙነት መድረክ በአዋጅ የተሰጣቸውን ስልጣንና ተግባር ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መነሻ ጽሁፍ የቀረበ ሲሆን፤ ተቋማዊ ብቃትን ለማሳደግ ሕጋዊ ውጤትን በግልጽ ማመላከት፣ ውሳኔዎችን ይፋ ማድረግ፣ የክትትል ሥርዓት መዘርጋት፣ የአፈጻጸም መለኪያዎችን ማዘጋጀትና የሥልጣን ወሰንን መለየት እንደሚገባ የሚመክሩ ሀሳቦች ቀርበዋል። የጉባኤው አባላት በቀረበው ሰነድና በተነሱ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ በዋና ዋና ነጥቦች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ጉባኤው ተጠናቋል። በዚሁ ጉባኤ ላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትን ጨምሮ በአዋጁ አንቀጽ 42 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት የተጠቀሱት የጉባኤው አባላት ተገኝተዋል። Previous Article አገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች መድረክ ተጠናቀቀ Next Article የፍርድ ቤቶች አመራሮችና ዳኞች በአርባምንጭ ከተማ የችግኝ ተከላ አካሄዱ Print 304