የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ጋር  የተቀናጀ አሰራርን መፍጠር የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ
/ Categories: News

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ጋር የተቀናጀ አሰራርን መፍጠር የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ጋር የተቀናጀ አሰራርን በመፍጠር የዳኝነት ስርዓቱን ይበልጥ ለማዘመን የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሟል።

‎‎ስምምነቱ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተቀናጀ የጉዳይ አስተዳደር መረጃ ስርዓት (iCMIS) ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት የዲጂታል ማረጋገጫና ምዝገባ ስርዓት ጋር እንዲተሳሰር በማድረግ፣ የሰነዶችን ትክክለኛነት በፍጥነትና በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ፣ የማጭበርበር ድርጊቶችን ለመከላከል እና ቀልጣፋ ዘመናዊ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው።

‎‎የመግባቢያ ሰነዱን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት እና የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ሐሚድ ኪኒሶ ተፈራርመዋል።

‎በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ክቡር ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት እንደገለጹት፤ ሁለቱ ተቋማት የሚያከናውኗቸው ሥራዎች ተመጋጋቢ በመሆናቸው በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ ልውውጥና የተቀናጀ የሥራ ሂደት መፍጠር የዳኝነት አገልግሎትን የበለጠ ቀልጣፋ፣ ግልጽና ተዓማኒ እንዲሆን ያስችለዋል ብለዋል።

‎የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ሐሚድ ኪኒሶ በበኩላቸው፤ የመግባቢያ ስምምነቱ መፈረም በተቋማቱ መካከል የሚደረጉ የመረጃ ልውውጦችን ለማጠናከር እና የሰነዶችን ደህንነት ለማስጠበቅ እንደሚያግዝ ገልፀዋል፡፡

‎‎አያይዘውም፤ በፍርድ ቤቱ እየተከናወኑ ያሉ የለውጥ ሥራዎች ለአገሪቱ የፍትሕ ሥርዓት መዘመን ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው በመግለጽ፣ በዳኝነት ዘርፍ የሚከናወኑ ሪፎርሞች ሌሎች አገራዊ የለውጥ ሂደቶችን በማፋጠን ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ተናግረዋል።

‎‎የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እያከናወነ ያለው የዲጂታላይዜሽን ሪፎርም፣ የአሰራር ለውጦች እና ዋና ዋና የቴክኖሎጂ ማሻሻያ ሥራዎች ዙሪያ ለሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ልዑካን ገለጻ የተደረገ ሲሆን፤ ከፊርማ ስነ ስርዓት በኋላ ልዑካኑ በፍርድ ቤቱ እየተተገበሩ ያሉ ዋና ዋና የሪፎርምና የዲጂታላይዜሽን ሥራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

Previous Article ለበጎ ፈቃደኛ ጠበቆችና የህግ አገልግሎት መስጫ ማዕከል አስተባበሪዎች የልምድ ልውውጥ መድረክ ተካሄደ
Next Article "የዋይድ ኤሪያ ኔትወርክ ፕሮጀክት የፍርድ ቤቶችን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ብቃት በከፍተኛ ደረጃ አሳድጓል፡፡" ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት
Print
539