Friday, August 28, 2026 / Categories: News የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች በቀጣይ የአምስት አመት የስትራቴጂክ ዕቅድ ረቂቅ ላይ ተወያዩ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክቡራን ዳኞች የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን የቀጣይ አምስት ዓመታት (2019-2023) የስትራቴጂክ ዕቅድ ረቂቅ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ አካሂደዋል። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ድሪባ ፈዬራ መድረኩን ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት፣ የምክክር መድረኩ ዋና ዓላማ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሚመሩበትን ስትራቴጂክ ዕቅድ ዳኞች ተወያይተውበት፣ ገንቢ ግብዓቶችን በማሰባሰብና ሰነዱን በማዳበር ወደ ሙሉ ትግበራ ለማስገባት እንደሆነ ገልጸዋል። የአምስት ዓመቱ የስትራቴጂክ ዕቅድ ረቂቅ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስትራቴጂክ ሥራ አመራር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አቤል ጌትነት የቀረበ ሲሆን፣ ሰነዱ ያለፈበትን ሂደት እና ዋና ዋና የትኩረት መስኮችን በዝርዝር አብራርተዋል። የዳኝነት ነፃነትና ግልጽነት፣ የዳኝነት አገልግሎት ቅልጥፍናና ጥራት፣ የዳኝነት አገልግሎት ተደራሽነት፣ የሰው ሀብት ልማትና ተቋማዊ አቅም፣ የላቀ የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ ኮሙኒኬሽን፣ ቅንጅታዊ አሠራርና ስትራቴጂያዊ አጋርነት የዕቅዱ ዋና ዋና የትኩረት መስኮች መሆናቸው በመድረኩ ተመላክቷል። በመድረኩ የተሳተፉት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች በቀረበው ረቂቅ ሰነድ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ ለዕቅዱ መዳበር ጠቃሚ ናቸው ያሏቸውን ሐሳቦችና አስተያየቶች ያቀረቡ ሲሆን፣ የተሰጡት ግብዓቶችም ሰነዱን ለማዳበርና ለማጠናቀቅ እንደሚውሉ በመድረኩ ተገልጿል። Previous Article የፌደራል ፍርድ ቤቶች እና ተጠሪ ተቋማት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄዱ Next Article የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመታዊ የሰራተኞች መድረክ መካሄድ ጀመረ Print 429