ለመገናኛ ብዙሃንና ባለሙያዎች ማስታወሻ

ማንኛውም ሰው ወይም ተቋም ወደ ፍርድ ቤት መግባትና በችሎት መታደም ይችላል፡፡ ይህ የፍርድ ቤት ውሎን ወይም አንድ የህዝብ ትኩረትን የሳበና የተለየ ጉዳይን ለመዘገብ ወደ ፍርድ ቤት የሚመጡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ያካትታል፡፡

የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን አስተተዳደራዊ ውሳኔዎንና የመረጃ ነጻነት ዓወጅ ቁጥር 590/2000 ድንጋጌዎችን መነሻ በማድረግ መገናኛ ብዙሃንና ባለሙያዎች (ጋዜጠኞች) የፍርድ ቤት ዘገባዎችን ለመስራትና መረጃ ለማግኘት ሊመሩባቸው የሚችሉ ማስታወሻዎች ተካቷል፡፡   

የመገናኛ ብዙሃንና ባለሙያዎች (ጋዜጠኞች) ሊያደርጓቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች

የፍርድ ቤት ወሎ ዘገባዎች አብዛኛው ህብረተሰብ በልዩ ሰሜት የሚከታተላቸው በመሆናቸው የመገናኛ ብዙሃንና ባለሙያዎች የሚሰሩት ዘገባ ከፍ ያለ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ የመገናኛ ብዙሃን እና ባለሙያዎች (ጋዜጠኞች) የፍርድ ቤት ዘገባዎችን በሚሰሩበት ጊዜ ከሌሎች ዘገባዎች ልዩነት በሚፈጥሩና እና የፍርድ ቤቱ መገለጫ የሆኑ እሴቶች ላይ አሉታዊም ሆነ አወንታዊ ተጽእኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ ምክያቶችን ለይተው ማወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የህግ ቃላትና ሐረጎች

የሚዲያ ባለሙያዎች (ጋዜጠኞች) የፍርድ ቤት ወሎን ለመዘገብ የግድ የህግ ዲግሪ እንዲኖራቸው አይጠበቅም፡፡ ነገር ግን ሪፖርቱን ለንባብ ለሚያቀርቡለት አንባቢ ወይም በሬዲዮና በቴሌቪዥን ለሚያሰናዱለት አድማጭ ተመልካች የፍርድ ቤት ስነስርዓቱንና የዳኝነት ሂደቱን እንዲሁም ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ብይን ወይም ትእዛዝ ትክክል መግለጽ እንዲችሉ የህግ ሙያዊ ቃላትንና ሃረጋትን ማወቅ እንዲሁም አጠቃቀማቸውን መረዳት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለሆነም ለፍርድ ቤት ውሎ እና የህዝብን ትኩረት የሚስብ በፍርድ ቤት እየታየ ያለ ጉዳይ ላይ ዘገባ ለመስራት የሚመጣ በተለይም አዲስ የሚዲያ ባለሙያ/ ጋዜጠኛ ዘገባውን ከመስራቱ በፊት መሰረታዊ የሚባሉ ህግና ዳኝነት ነክ የሆኑ ቃላትን እንዲያውቅ/ እንዲለይ ይመከራል፡፡

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አደረጃጀትን መረዳት

የፌዴራል መንግስትን ከመሰረቱት ሶስት አካላት መካከል አንዱ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ናቸው፡፡ እዚህም የፌዴራል ጠቅላይ የፍርድ ቤት ፣የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ እና የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ናቸው፡፡ ፍርድ ቤቶቹ በፌዴራል መንግስት ስር በመደራጀታቸው አንድ ቢሆኑም ስልጣንና ሃላፊነታቸው የተለያየ ነው፡፡ በመሆኑም የፍርድ ቤት ውሎንና በፍርድ ቤት እየታየ ያለ ጉዳይን መሰረት በማድረግ ማንኛውንም ዘገባ የሚሰሩ ባለሙያዎች ፍርድ ቤቶች በሙሉ አንድ አይነት አለመሆናቸውን መረዳትና ጉዳዩን እየተመለከተ ያለው ፍርድ ቤት የትኛው እንደሆነ በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል፡፡

የገለልተኝነት መርህ

ፍርድ ቤቶች ራሳቸውን ችለው ነጻና ገለልተኛ ሆነው የተቋቋሙ ተቋማት ሲሆኑ ዳኞች ለየትኛውም አካል ውግንና ሳይቆሙ በገለልተኝነት ዳኝነት መስጠት የሙያቸው ስነምግባር ግዴታ ይጥልባቸዋል፡፡ ዳኞች ዳኝነት እንዲሰጡበት በቀረበላቸው ጉዳይ የጥቅም ግጭትና የዳኝነትን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ሊያስገባ የሚችል ጉዳይ በገጠማቸው ጊዜ ጉዳዩን ከመመልከት ራሳቸውን ያቅባሉ/ያገላሉ፡፡  በተመሳሳይ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች (ጋዜጠኞች) የፍርድ ቤት ውሎን ወይም በፍርድ ቤት የተያዘና እልባት ያላገኘ ጉዳይን በሚዘግቡበት ግዜ ዘገባቸው ከግል አስተያየታቸውና ፍላጎታቸው የጸዳ መሆን አለበት፡፡ 

የፍርድ ቤቱን የመረጃ ምንጭ መጠቀም

የዳኝነት ሙያ የስነምግባር ደንብ መሰረት የፌዴራል ዳኞች በሚመለከቷቸውና በሂደት ላይ ባሉ በየትኛውም ጉዳዮች ቃለ መጠይቅ አይሰጡም፡፡ ዳኞች አስተያየታቸውንና ውሳኔያቸውን የሚገልጹት በግልጽ ችሎትና በውሳኔ ጽሁፋቸው ነው፡፡ ስለሆነም ጋዜጠኞች ለዘገባቸው የሚሆናቸውን መረጃ በቀጥታ ችሎት በመታደም እና ከውሳኔ ግልባጭ ብቻ መሰብሰብ ይችላሉ፡፡ 

የመገናኛ ብዙሃን እና ባለሙያዎች (ጋዜጠኞች) ክልከላዎች

ከፍርድ ቤቱ አስተዳደራዊ አቋሞችና ከመረጃ ነጻነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 አንጻር ከታች የተገለጹት ተግባራት የተከለከሉ ናቸው፡፡

  • በችሎት ውስጥ ፎቶ ግራፍ የማንሳት፤ ቪዲዮ የመቅረጽ እና የችሎት ሂደቱን በድምጽ መቅረጫ መቅዳት አይቻልም፡፡
  • ማንኛውንም ቀረጻ ለማድረግ የሚያገለግሉ መሳሪያዎችን ለጥበቃና ጸጥታ ባለሙያዎች ሳያሳውቁ ወደ ፍርድ ቤቱ መግባት አይፈቀደም፡፡ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ወደ ጊቢው ይዞ መግባት ቢቻል እንኳን ፈቃድ ሳያገኙ ቀረጻ ማካሄድ የተከለከለ ነው፡፡ 
  • በፍርድ ቤቱ በመታየትና እልባት ባገኘ ጉዳይ ላይ ዳኞችንና በፍርድ ቤት አስተዳደራዊ እርከኖች ላይ የተሾሙም ሆነ የተመደቡ ሃላፊዎችን ቃለ መጠይቅ ማድረግ አይፈቀድም፡፡
  • በግልጽ በሚታወቅና በህግ በሚፈቀድ ምክንያት ችሎት በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ዝግ ሊሆን ይችላል፡፡ ችሎት ሙሉ በሙሉ ዝግ በሚሆንበት ጊዜ ባለጉዳዮች ብቻ ክርክራቸውን የሚያደርጉበት ሲሆን በከፊል ዝግ ሲሆን ከባለጉዳዮቹ በተጨማሪ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተለይተው የሚታደሙበት ነው፡፡  አንድ ጉዳይ በዝግ ችሎት እንዲታይ ችሎቱ ውሳኔ በሰጠ ጊዜ የሚዲያ ባለሙያዎች ቢሆኑም አንኳን ወደ ችሎቱ እንዲገቡ አይፈቀድም፡፡ ክልከላውን በተመለከተ በሪጂስትራር በኩል መረጃ በማግኘት ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡ 

መገናኛ ብዙሃንና ባለሙያዎች (ጋዜጠኞች) መረጃ ማግኘት የሚችሉባቸው ሁኔታዎች

የመረጃ ነጻነት ዓዋጅ ቁጥር 590/2000 ድንጋጌን መሰረት በማድረግ ከታች በተገለጹት አግባብ ፍርድ ቤት ነክ መረጃ ማግኘት የሚቻልባቸው ሁኔታዎች አሉ፡

  • ማንኛውንም ቀረጻ ለማከናወን የሚቀርብ ጥያቄ በፍርድ ቤቱ አስተዳደር አስፈላጊነቱ ከታመነበት፤ በኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬትና እና በሬጂስትራር ጽ/ቤት በኩል ቀረጻ ለሚካሄድበት ችሎት ጥያቄው ቀርቦ ዳኞች ሲፈቅዱ ብቻ የሚከናወን ይሆናል፡፡
  • አስተዳደራዊና አሰራርን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ የሚቀርቡ የመረጃ ጥያቄዎች በፍርድ ቤቱ የበላይ አመራሮች ሃላፊነት በተሰጠው ሃላፊ መረጃው እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡
  • ፍርድ ቤት ቀርበው በመታየትና እልባት በተሰጠባቸው ጉዳዮች ላይ ግንኙነት ያላቸውን መረጃዎች/ ሰነዶች ለማግኘት በሚቀርብ ጥያቄ መሰረት በፍርድ ቤቱ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬትና በሬጂስትራር ጽ/ቤት አማካኝነት ጉዳዩ ከሚመለከተው መዝገብ ማግኘት ይቻላል፡፡   
  • በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ሌሎች አካላት በፍትህ ስርዓቱ ላይ ለሚደረጉ የጥናት ስራዎች ከፍርድ ቤት የሚፈለጉ መረጃዎችን ለኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት በሚቀርብ ጥያቄ ስታትስቲካል (ቁጥር ነክ) መረጃ፤ የአፈጻጸም ሪፖርቶች፤ የወሳኔ ግልባጮችና የመሳሰሉትን መረጃዎች ማግኘት ይቻላል፡፡