የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በሕገ መንግስቱ እና በሕግ በተሰጣቸው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት የሚቀርቡ ጉዳዮችን በማስተናገድ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን፣ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲጠበቁ ሰላም እና ስርዓት እንዲከበር የማድረግ ተግባራትን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡
በዚህ መሰረት በ2015 በጀት ዓመት በነበረዉ የመዛግብት አፈጻጻም አንጻር ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች በአጠቃላይ 213,116 መዛግብት ቀርበዋል። ከእነዚህም ዉስጥ ለ184,467 (86.56%) መዛግብት እልባት መስጠት የተቻለ ሲሆን 28,675 (13.44%) መዛግብት ደግሞ ወደ 2016 በጀት ዓመት ተሻግረዋል፡፡ የበጀት ዓመቱ አፈጻጸም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ2014 በጀት ዓመት ለፌ/ፍ/ቤቶች የቀረቡት 209,317 መዛግብት ሲሆኑ ዕልባት ያገኙት ደግሞ 176,767 ነበሩ፡፡ በዚህም መሠረት በ2015 በጀት ዓመት የቀረቡት መዛግብት በ2014 በጀት ዓመት ከቀረቡት በ3,799 (1.8%) ከፍ ያሉ ሲሆን በተመሳሳይ ዕልባት ያገኙትም በ7,670 (4.3%) መዛግብት ከፍ ያሉ ናቸው፡፡