በፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በፌደራል የዳኝነት አካል ዉስጥ ስለሚታዩ የሙስና ተግባራት መከላከያና መቆጣጠሪያ ማስፈጸሚያ ደንብ ስለመደንገጉ የተሰጠ መግለጫ

Solomon Ejigu 0 572

ፌደራል ፍርድ ቤቶች ባለፉት አራት ዓመታት ነጻ፣ ቀልጣፋ ፣ ዉጤታማ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎች የማሻሻል፣ አሰራርና ስርዓቶችን የመዘርጋትተግባራትን ሲያከናዉኑ ቆይተዋል፡፡ በእነዚህ ዓመታት የተገኙ ዉጤቶች በማህበረሰቡ ዕዉቅና ያገኙ እና እያደር እየጎለበቱ ሊሄዱ የሚገቡ ናቸዉ፡፡

ፍርድ ቤት ፍትህን የመስጠት ኃላፊነት በህገ-መንግስትና በህግ የተሰጠዉ አካል ሲሆን በዚህ አካል ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለይቶ ስርዓትን በተከተለ መልኩ አፋጣኝ እርምጃዎችን መዉሰድ ይገባል፡፡ በማህበረሰቡ በተደጋጋሚ ከሚነሱ ቅሬታዎች ዉስጥ አንዱ በተወሰኑ ዳኞች የሙስና ተግባራት የሚፈጸሙ መሆናቸዉ ነዉ፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሙስና ተግባራት ላይ ያለዉ ፖሊሲ "በምንም ሁኔታ ተቀባይነት የሌለዉ ተግባር" የሚባለዉ ሲሆን በሙስና ተግባር ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች የዳኝነት ስርዓቱ በሚፈቅደዉ አግባብ ተጠያቂ እንዲሆኑ በጥብቅ ይፈለጋል፡፡ በዚህም ምክንያት የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በዳኝነት አካል ዉስጥ የሚታዩ የሙስና ተግባራት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ስትራቴጂ አዉጥቷል፡፡ ይህንም ስትራቴጂ ለማስፈጸም የሚያስችል ደንብ ነሐሴ 9 /2014 ዓ.ም አጽድቋል፡፡