የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉባዔ በፌዴራል ፍ/ቤቶች አዋጅ 25/88 ከአንቀጽ 31-34 በተደነገገው መሰረት የተቋቋመና በዳኝነት ሥራ አስተዳደር ረገድ በሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ ተወያይቶ መፍትሔ የመስጠት፤ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አሰራርን ለማሻሻል የሚረዱ መመሪያዎችና ውሳኔዎችን የማሳለፍ፤ አዳዲስ ሕጎች እንዲወጡ ወይም ነባር ሕጎች እንዲሻሻሉ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሃሰብ የማቅረብ፤ የዳኝነት ስራ አካሄድን ለማቀላጠፍና ለማጠናከር የሚረዱ ሌሎች ተግባራትን የማከናውን እና ለጉባዔው ስራ አፈጻጸም አስፈላጊውን ደንብ የማውጣት ስልጣንና ተግባር የተሰጠው ጉባዔ ነው፡፡ በዚህም መሰረት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉባዔ 5ኛውን ዓመታዊ ጉባዔ ዛሬ ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም በፌዴራልና በክልል ፍርድ ቤቶች ተቋማዊና ዳኝነታዊ ነጻነት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡